Wed. Jan 27th, 2021

Ethiopian Intercept

We Share News

በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ ከዳያስፖራው 100.7 ሚሊዮን ብር ተሰበሰበ

በትግራይ ክልል የተከናወነውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ በክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመመለስና የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረግ መንግሥት ያቀረበው አገራዊ ጥሪን መሠረት በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ከውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን እስካሁን ድረስ 100.7 ሚሊዮን ብር እንደሰበሰበ አስታወቀ፡፡

ይህ የተገለጸው በትግራይ ክልል ከሕግ ማስከበር ጋር በተያያዘ የተፈናቀሉ ሰላማዊ ዜጎችን ለመርዳት፣ በአገረ እንግሊዝ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሦስት ሳምንታት ሲካሄድ በቆየው የበይነ-መረብ የገቢ ማሰባሰበያ ዝግጅት መሆኑም ተነግሯል፡፡ ይህም የተነገረው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንዲሁም በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተሳተፉበት የበይነ-መረብ ውይይት ሰኞ ጥር 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በተጠናቀቀበት ወቅት ነው፡፡

መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደውን ሕግ የማስከበር ዕርምጃ መጠናቀቅን ተከትሎ በአፋጣኝ የመልሶ ማቋቋም መርሐ ግብር በመንደፍ ወደ ተግባር መግባቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይቱ ላይ አስታውቀዋል።

‹‹ኢትዮጵያን በፈለግናት መንገድ ብቻ ልንዘውራት፣ ልንቃኛት ይገባል›› የሚሉ ኃይሎች፣ ለውጡን በመገዳደር እስከመጨረሻው ድረስ የተፋለሙበት ሒደት እንደሚታወቅ የጠቆሙት አቶ ደመቀ፣ አሁን በአገራችን ችግሩ በተፈጠረበት አካባቢ እየተሠራ ያለው ዋና ሥራ የማቋቋምና ሰብዓዊ ዕርዳታ የማቅረብ ሥራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ዳያስፖራው በሰላም ግንባታ፣ በማኅበራዊ ዘርፍ፣ በኢኮኖሚ፣ በባህልና በቱሪዝም በተናጠልም ሆነ በጋራ የአገሪቱን ዕድገትና ብልፅግና በመተባበር እንዲያፋጥን ምቹ ሁኔታዎች መፍጠራቸውንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኤምባሲዎች አስተባባሪነት በዚህ መልኩ ወገኖቻቸውን ለመደገፍና ለማቋቋም የገንዘብ ማሰባሰብ ተግባር ማካሄዳቸው የሚመሰገን ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው፣ በብሪታኒያ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል አገራቸውን ለመደገፍ የገንዘብ፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ አሁንም የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት ለሚያደርጉት ጥረት ምሥጋና አቅርበዋል።

በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች ዙሪያ ለሦስት ሳምንታት የተደረገውን የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ጨምሮ በህዳሴ ግድብ የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ፣ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ለቀረበው ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት በገንዘብና በሕክምና መሳሪያዎች ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ እንዳሉት ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራው በተቀናጀ መልኩ በሁሉም አቅጣጫ ተጠናክሮ ቀጥሏል፣ ዕርዳታ ማሰባሰብ ከዘር፣ ከሃይማኖትና ቋንቋ ጋር የማይገናኝ ተግባር መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ መንግሥት በአሁን ሰዓት በትግራይ ክልል ለ2.2 ሚሊዮን ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ መልካም ሐሳብ ተብሎ ከዳያስፖራው የተሰባሰበውን ሀብት ምን ላይ እንደዋለ በተለያዩ የግንኙነት አማራጮች እንደሚያሳውቁ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላም ዳዊት በበኩላቸው በውጪ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገሪቱ ለሚያጋጥማት የተለያዩ ችግሮች ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል ብለዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ለህዳሴው ግድብ በቦንድ ግዢና በጥሬ ድጋፍ 76 ሚሊዮን ብር፣ ለኮቪድ-19 ድጋፍ 200 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በትግራይ ክልል የተደረገውን የሕግ ማስከበር ተከትሎ ላጋጠመው የሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፍ 100.7 ሚሊዮን ብር በተለያዩ አገሮች ከሚገኙ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ተሰብስቧል ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩ ኤን ኤች ሲ አር) ባሳለፍነው ሳምንት እንዳስታወቀው ከትግራይ ክልል ብቻ ካለፈው ኅዳር ወር ጀምሮ 56,000 ዜጎች ተፈናቅለው ወደ ሱዳን መጋግባታቸውን፣ ከ222 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በአገር ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው እንደሚገኙ ገልጾ፣ እንደ ምግብ፣ ውኃ፣ መጠለያና የሕክምና ድጋፍ በአፋጣኝ ሊደረግላቸው እንሚገባ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ሪፖርተር

Subscribe To Our Newsletter

[mc4wp_form id="318"]