Sun. Jan 17th, 2021

Ethiopian Intercept

We Share News

‹‹ የሚጠልሁን ሰዎች ከማጥፋት የሚጠሉብህን ነገር አጥፋ››

የደሃ አባት፣ ዘመናዊነትን ናፋቂ፣ ሰው አክባሪ፣ በጥበብ ኗሪ ይሏቸዋል፡፡ እንደ ተራራ ገዝፎ ይፈራ የነበረውን የነጭ ሰራዊት ገርሰሰው የጥቁር አብዮት የቀሰቀሱ፤ ለሀገራቸው ወደኋላ የማይመለሱ፤ ኢትዮጵያ ተቀምጠው በመላው ዓለም በሚገኘው ጥቁር ልብ ውስጥ በፍቅር የነገሡ ኃያል ናቸው፡፡

በጭንቅ ዘመን የተገኙ፣ ጥቁርን እኩል ሰው ያሰኙ ናቸው፡፡ ፈጣሪ የአፍሪካ የጨለማ ዘመን ይጠናቀቅ፣ የአውሮፓውያን ኃያልነት ይወደቅ፣ የግፍ ዘመናቸውም ይለቅ ሲል ምኒልክን በኢትዮጵያ ላይ አነገሳቸው፡፡ ጣልያንንም ለምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ላካት፡፡

በምኒልክ መሪነት፣ በኢትዮጵያዊያን ቆራጥ አርበኝነት የጣልያን ኃያልነት አድዋ ላይ ተገረሰሰ፡፡ የአውሮፓውያን የረጋው የቀኝ ገዢነት ጉልበትም ተንቀሳቀሰ፡፡ ከአድዋ በኋላ ዓለም ጨለማ ብቻ የምትመስላቸው ጥቁሮች ሁሉ ብርኃን የሚባል ሌላ መልክ እንዳላት ተረዱ፡፡ በአድዋ መነሻነት ጥቁሮች ሁሉ ለነጻነታቸው መዋደቅ ጀመሩ፡፡

ቀስ በቀስም ነጻነታቸውን አወጁ፡፡ የአድዋውን ጀግና እምዬ ምኒልክን ግሊከን የተባለ ፀኃፊ ‹‹ምኒልክ በጥበብ ሕዝብን ሲያስተዳደር ሕዝቡ በፍቅር እንዲከተለው እንጂ በፍርሐት እንዲገዛለት አይፈልግም፡፡ በዚህም ምክንያት በማስተዳድሩ በኩል የወጣለት ጥሩ መሪ ነው›› ብሏል፡፡

ኡላንዶርፍ የተባለው ፀሐፊ ደግሞ ‹‹ በምኒልክ ዘመን የአገሪቱ ክብር አደገ፤ የዘመናዊ አስተዳደር መሠረትም ተጣለ፡፡ ንጉሡም በዘመናዊ አስተዳደር ይመራሉ›› ብሏቸዋል፡፡ ሮድ የተባለው ፀሐፊ ‹‹በምኒልክና በሕዝቡ መሀል ርቀት የለም›› ሲል ምን ያክል ለሕዝቡ ቅርብ የነበሩ መሪ መሆናቸውን መስክሯል፡፡

ምኒልክ በአስተዳደር በኩል ዘዴኛ ነበሩ፤ ምንጊዜም ቢሆን ጠላቶቻቸውን በፍቅር ለመሳብና የፍቅር ምርኮኛ ለማድረግ የሚጥሩ እንደነበሩም ይነገርላቸዋል፡፡ ‹‹የሚጠልሁን ሰዎች ከማጥፋት የሚጠሉብህን ነገር አጥፋ›› የሚለው አባባል የሚገዛቸው እንደነበረም ነው የሚነገርላቸው፡፡

ታሪክ አጥፊ የዘመኑ ፖለቲከኞች እንደሚሏቸው ምኒልክ ጨካኝ ሳይሆኑ አዛኝ እንደነበሩም ሥራዎቻቸውን እያጣቀሱ የታሪክ ሰዎች ዘክረዋቸዋል፡፡ አዛኝ ከመሆናቸው የተነሳ ጦርነት ገጥሟቸው የማረኩትን ደም ጠርገው፣ ከወጌሻ አድርሰው፣ አብልተው፣ አጠጥተውና አስታመው የሚያድኑ ናቸው፡፡ በአድዋ ጦርነት ወቅት በታላቅ ተጋድሎ የማረኳቸውን የጣልያንን ወታደሮች እንደራሳቸው ሰራዊት እንደተንከባከቧቸው ታሪክ ያስረዳል፡፡

ምኒልክ ደሃን ስለሚወዱ ደሃው የደሃ አባት ይላቸው ነበር፡፡ ግብር ሲያበሉ እንኳን የሚጀምሩት ከደሃው ነበር፡፡ በምኒልክ ከእሁድ በስተቀር በሌላው ቀን ሶስት ሺህ የሚደርስ ሰው ግብር ይበላ ነበር ይባላል፡፡ እሁድ ቀን አራት ሺህ የሚደርስ ሰው ግብር ያበሉ ነበር፡፡ በግብር ሰዓት መጀመሪያ ግብር የሚበሉት ዘበኞች ነበሩ፡፡ ዘበኞች በልተው ለጥበቃ ሲወጡ ቀሳውስቱ እንዲበሉ ይደረጋሉ እንጂ ግብር ከመኳንንቱ እንዲጀምር አይፈቅዱም ነበር ይባላል፡፡ ምኒልክ ከእሳቸው በፊት አሽከሮቻቸው ምግብ እንዲበሉ የሚያስቀድሙ፣ ፈረሱን ከአሽከሮቻቸው ተቀብለው አሽከሮቹ ቀድመው እንዲበሉም ያድርጋሉ፡፡

ጣልያናዊው ደ. ካስትሮ ‹‹ በዓለም ላይ ያሉ ትልቅ ተራማጅ ሰው ናቸው፤ ከሰማይ ፕላን ወርዶ ከመሬት ጨረቃ ድረስ የሚያደርስ የመገናኛ ፕላን ነው ቢሏቸው ንጉሡ የሚቻል ከሆነ እንስራው የሚሉ ናቸው›› ብሎላቸዋል፡፡ ገናናው ንጉሥ በአንድ ወቅት በኤደን የሚኖር ወዳጃቸው የሆነ ነጋዴ ጠቢባን ወደ ሀገራቸው እንዲያመጣላቸው ወደ ሲውስ (ሲውዝ) ላኩትና ሶስት ጠቢባን አመጣላቸው፡፡ ከመጡት ጠቢባን መካከል የዙሪክ ፖሊ ቴክኒክ ምሩቁ አልፍሬድ ኢልግ አንዱ ነበር፡፡

በዚያ ወቅት የነበረው ኢልግ እንዲህ ሲል ጉዳዩን መዝግቦታል ‹‹ ከንጉሡ ጋር ለመተዋወቅ ንጉሡ ዘንድ ገባን፡፡ ንጉሡም መሀንዲሶች መሆናችንን ሰምተው ነበርና በደስታ ከተቀበሉን በኋላ አዛዣቸውን ጠርተው ለእነዚህ ሰዎች አንድ የሚያድሩበት ክፍል ስጥልኝ፤ ከዚያም ቆዳና ወስፌ ስጣቸው፡፡ እናንተም እንግዲህ ለጠዋት ሁለት ጫማ ሰፍታችሁ እንድታመጡልን አሉን፡፡ እኛም ከዚያ ከተሰጠን ክፍል ሆነን የማናውቀውን የጫማ መስፋት ሥራ እናጠና ጀመር፡፡ ያንዳችንን ጫማ ስፌቱን ቀዳደን በዚያ ልክ ቆዳ ስንቆርጥ አደርን፡፡

ጠዋት ምኒልክ አስጠሩን የታለ የሰፋችሁት ጫማ አሉን፡፡ እኛም የእኛ ሙያ ታላላቅ መንገዶችንን እና የባቡር ሃዲዶችን መሥራት ነው እንጂ ይሄን ትንንሽ ነገር አናውቅበትም አልናቸው፡፡ ምኒልክም ራስህ የምትሄድበትን ጫማ መሥራት ያልቻልክ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሄድበትን መንገድ መሥራት እንዴት ትችላለህ አሉንና ጠመንጃ መሥራትስ ትችላላችሁ? ኡሉን፡፡ እኔም ምን ማለትዎ ነው? ጠመንጃ እኮ የሚሰራው በፋብሪካ ነው፤ ፋብሪካ ደግሞ በብዙ ገንዘብ ተገዝቶ የሚመጣ ነው አልኳቸው፡፡

ምኒልክም ይሄን ማወቅህ ደህና ነው አሉን›› ሲል ጥበብን እንዴት ይወዱ እንደነበርና እንዴት ይፈትኑ እንደነበር ተናግሯል፡፡ በዚያ ዘመን የማይታመን የሚመስል ታሪክ የሰሩት ኃያሉ ንጉሥ ምኒልክ ‹‹ እምዬ›› የሚለውን ጣፋጭ ሥማቸውን ከማይጠፉ ጣፋጭ ስራዎቻቸው ጋር ጥለውልን ወረኃ ታኅሣሥ በገባ በሦስተኛው ቀን ይችን ምድር ተሰናብተዋታል፡፡

እንደ ምኒልክ ሁሉ ጠቢብ ሁኑ፤ ከበቀል ይልቅ ይቅርታና ፍቅር ይግዛችሁ፡፡ በፍቅር የተዋጄ ሀገር በፍቅር የተመላ ትውልድ ይፈጥራል፡፡ በበቀል የተዋጄ ሀገርም መከራ ይዞ ይመጣል፡፡ ኢትዮጵያን ፍቅር ያላብሳት፡፡ መልካም ሁሉ ይሁን፡፡ ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ እና ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ ዓፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት የሚለውን በምንጭነት ተጠቅሜያለሁ፡፡
በታርቆ ክንዴ፣ አማራ ማስ ሚዲያ

Subscribe To Our Newsletter

[mc4wp_form id="318"]