Sun. Jan 17th, 2021

Ethiopian Intercept

We Share News

ወታደሮችን በሲኖ ትራክ እስከመጨፍለቅ የዘለቀው የጁንታው የክፋት ጥግ

ሃምሳ አለቃ ደረጀ አንበሳ በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ የጥገና ባለሙያ ናቸው። በሙያቸው አገራቸውን ሌት ተቀን ከማገልገላቸውም በላይ እንደማንኛውም የመከላከያ አባል ትግራይ ህዝብ በችግሩ ጊዜ ከጎኑ በመቆም አጋርነታቸውን ሲገልጹ ኖረዋል። የህዝብና የአገር ከለላና መከታ የሆነው የኢፌዴሪ መከላከያ አባል እንደመሆናቸው አንድም ቀን በአገር ልጅ የባንዳነት ተግባር ይፈጸምብኛል ብለው አስበውም አያውቁም።

ይሁንና በእናት ጡት ነካሾች ጥቅምት 24/2013 ከምሽቱ አራት ሰዓት ያልታሰበ ጥቃት ተፈጸመባቸውና ያለምንም ጥፋታቸው ተይዘው ለእስር መዳረጋቸውንና ቀላሚኖ እሰርቤት መታሰራቸውን ይገልጻሉ።

“ከቀላሚኖ እስር ቤት ወደ አግቤ በመቀጠልም ከትንሽ ቀን በኋላ ወደ ተንቤን መምህራን ኮሌጅ ወሰዱን። የመከላከያ ሠራዊትን የከባድ መሳሪያ ድምፅ ሲሰሙ የ90 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ አስጀመሩን። ልክ 40 ኪሎ ሜትር እንደተጓዝን ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ ሲኖ ትራክ መኪና ከኋላችን መጣ። ተጓዡ ወደ 1,200 ሰው ነበር። ከአስፋልት እንድንወጣ ካለመፈቀዱም በላይ ከአስፋልቱ መሀል ከወጣን ልዩ ሀይል ተኩሶ ይመታን ነበር። ከግራና ከቀኝ ገደላማ የሆነ ጠባብ ቦታ ላይ ስንደርስ ሲኖ ትራክ መኪና ልከው ከኋላችን ነዱብንና የሚገድለውን እየገደለ፣ ያቆሰለውን እያቆሰለ ሄደብን።

እኔንም አንድ እግሬን አገኘኝና እግሬ ከተሰበረ በኋላ ተንከባልዬ ጉድጒድ ውስጥ ገባሁ። እዚያው ጉድጓዱ ውስጥ ከተጎዱ ጓደኞቼ ጋር ተኝቼ አደርኩ። ሲኖ ትራኩ ቢያንስ እስከ 50 ሜትር የተጓዘው በሰዎች ላይ ነበር። በዚህም ግማሹ ሞተ፣ ግማሹ ቆሰለ የቀረውም ወደገደል ገባ። እንግዲህ የራሳችን ወገን ነው እንዲህ አይነት በደል የፈፀመብን። ይህ ደግሞ በጣም የሚያሳዝን ድርጊት ነው። ስንት ዓመት ሙሉ አብረናቸው ኖረን በመኪና ሲጨፈልቁን በጣም ነው የተሰማኝ፤ በጥይት ቢገድሉኝ ይሻል ነበር” ይላል::

በወቅቱ ሴቶችም ህፃናትም አብረውን ነበሩ ማን እንደሞተ ማን እንደተረፈ አንኳን አላውቅም ያለው ወታደሩ “በወቅቱ በሕይወት የተረፋትም ተበታተኑ፤ አንዳንዶቹም ቆስለው ወደጫካው ገቡ፤ የሞቱትም እዛው ቀሩ አምስት የምንሆን ሰዎች እዛው አድረን ከሞቱት ሰዎች መሀል በሕይወት ወጣን። የሞቱ ልጆችን እንኳን ለመለየት አልቻልኩም፤ አጠገቤ ነው እየጮሁ የሞቱት፤ ምንም ልረዳቸው አልቻልኩም። በወቅቱ እኔም በሁለት እግሬ መቆም አልችልም ነበርና በጉልበቴ ዳዴ እያልኩ ነው የወጣሁት” ሲል የውቅቱን አሳዛኝ ሁኔታ ይገልፃል::

“እኛኮ ከሌሊቱ 11 ሰዓት እየተነሳን አጨዳ የምናጭድ፤ ኮረና ገባ ሲባል ብር እያዋጣን የምንደግፍና ከደሞዛችን እየቆረጥን የልማት ስራዎችን የምንሰራ ነን። እኛ ለትግራይ ህዝብ ልማት ወደኋላ ብለን አናውቅም። ይሁንና ጁንታውና የእሱ ተላላኪዎች በሰው ላይ የማይፈፀም ድርጊት ነው የፈፀሙብን። ሰብስበው በቦንብ ቢያቃጥሉን ወይም በጥይት ቢገድሉን ይሻል ነበር። የውጪ ጠላት እንኳን በመኪና ሰውን ደፍጥጦ አይገድልም። ድርጊቱ ከተፈፀመብን በኋላ በመኪና መንገድ ላይ ስንሄድ እየተሸማቀቅን ነው። ጭንቅላታችን ራሱ ተጎድቷል::

ሌላው ተመሳሳይ ድርጊት የተፈፀመበት አምሣ አለቃ ወንድማገኝ ወልደገብርኤል ነው። እሱ እንደሚገልፀው በልዩ ሀይል እና በሚሊሻ ታጅበን በእግር እየተጓዝን ሳለ ከአስፓልቱ እንዳትወጡ አሉን እኛም ፈንጂ ያለ መስሎን የአስፋልቱን መሀል ይዘን መጓዝ ጀመርን። ጨለምለም ሲል ከኋላችን ሲኖትራክ መኪና መጣ፤ ከፊት ለፊት ተኩስ ተከፈተብን፤ እንዳንመታ ብለን ሁላችንም ተኛን፤ በዚህ ወቅት ሲኖ ትራኩ እየጨፈለቀን ሄደ ።

ግማሹ እየተንከባለለ ወደገደል ገባ፤ ተገጭተን የተረፍነው በማግስቱ ተነሳን፤ ብዙዎች ግን በሚያሳዝን ሁኔታሞቱ፤ አንዳንዶቹም ቆሰሉ፤ አሽከርካሪው ለመትረፍ የሚሞክሩ ሰዎችንም ዚግዛግ እየነዳ ነበር ሲጨፈልቃቸው የነበረው። በእግራችን መሄድ አቅቶን ጅብ ይብላን ብለን እዛው ከተኛን በኋላ ታፍነው በመከላከያ ሰራዊት እርዳታ የተለቀቁ እስረኞች እየረዱን የተወሰነ ርቀት ከተጓዝን በኋላ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ደርሰው ወደዚህ አመጡን። ሲሉ ደረሰባቸውን ግፍ አስረድተዋል።

Subscribe To Our Newsletter

[mc4wp_form id="318"]