Wed. Jan 27th, 2021

Ethiopian Intercept

We Share News

አፍሪካዊ ድሮኖች

ሕወሓት “አፍሪካዊ ባልሆነ ድሮን ተደበደብኩ” በማለት የምታሰማውን አቤቱታ በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው። አንዳንዶች ራሷ ሕወሓት ” አሰብ ከሚገኘው የዐረብ ኢምሬቶች የጦር ማዕከል በሚነሱ ድሮኖች ተደበደብኩ” ያለችውን በመመርኮዝ የአቡዳቢ ድሮኖች ማለቷ ነው ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ አፍሪካ ውስጥ ባልተገጣጠሙ ድሮኖች ተቀጠቀጥኩ ማለቷ ነው ይላሉ።

አንድ ነገር ግን ርግጠኛ ሆኖ ለመናገር ከ9 ዓመታት በፊት እስራኤል ሰራሽ ድሮኖችንን ከእስራኤሉ የድሮኖች አምራች ከሆነው ብሉበርድ ኤሮ ሲስተም ድሮኖችን የገዛች ራሷ ሕወሓት ናት። ሕወሓት በወቅቱ የብሉበርድ ዘመናዊ ምርቶች የሆኑትን ቡመራንግና ስፓይላይት ድሮኖችን ከመግዛትም ባለፈ በአገር ውስጥ የድሮኖች መገጣጠሚያ ፕላንት እንዲሰራላትም ከአምራች ኩባንያው ጋር ተዋውላ ነበር። በወቅቱም የምሥራቅ አፍሪካዋ ኡጋንዳ ከሌላው የእስራኤል የመከላከያ መሳሪያዎች አምራች ከሆነው ኤሮኖቲክስ (Aeronautics Defence Systems) ኦርቢተር ኤር ቬሂክል መግዛቷም ይታወቅ ነበር።

ኤሮኖቲክስ ከኡጋንዳም አስቀድሞ ለሌላዋ አፍሪካዊት ሃገር አንጎላ እንዲሁ የተለያዩ ድሮኖችን ሸጦ ነበር። አንጎላ ከሌላው የእስራኤል ኤሮስፔስ ተቋም (Aerospace Industries (IAI) ሄሮን የተሰኙ ድሮኖችን ጨምራ ገዝታ ነበር። ሄሮንን ጎረቤታችን ኬንያም ከዚሁ ተቋም ገዝታለች።

ከዚህ በላይ ያሉት የድሮንና የሌሎች የኤሮስፔስ ኢንዱስትሪ ምርቶች በአህጉራችን የተለያዩ ሃገራት እጅ የገቡት ከ 8 ዓመታት በፊት ነው። በአሁኑ ሰዓት በርካታ የአህጉራችን ሃገራት አየር ኃይል ተቋማት የድሮን ባለቤቶች መሆናቸው ይታወቃል። ሕወሓት ራሷ ባቋቋመችውና በሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ይመራ በነበረው የመከላከያ ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ( ሜቴክ) በኩል የድሮኖች መገጣጠሚያ ፕላንት እንዳቋቋመችም ስትነግረን ነበር።

ከ 5 ዓመታት በፊት “የኢትዮጵያ መከላከያ ኢንዱስትሪ በሚያስደንቅ ሁኔታ አነስተኛ የሆኑ የቅኝትና የስለላ ተግባርን የሚፈጽሙ ዘመናዊ ካሜራና መረጃ ማስተላለፊያ ያላቸው ከእይታ በጣም ርቀው ከ18,000 ጫማ በላይ በሰማይ በመብረር ተፈላጊውን መረጃ የሚያጠናቅሩ ሰው አልባ ድሮኖችን ሰርቷል” የሚል ዜና በሁሉም መንግሥታዊ የመገናኛ ብዙኃን ተስተጋብቷል።

በአጭሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአህጉራችን የመከላከያ ተቋማት ድሮን ከመታቅ አልፈው እንደሚገጣጥሙም ቢነገርም፤ የዓለማችን ድሮኖች ዋና ዋና አምራቾቹ አሜሪካና እስራኤል መሆናቸው አይካድም። ናይሮቢም ሆነች ካይሮ፣ ፕሪቶሪያም ሆነች ሪያድ ድሮንን ገዢዎች ቢበዛም ገጣጣሚዎች እንጂ አምራቾች አይባሉም። ሕወሓት “አፍሪካዊ ያልሆኑ ድሮኖች” ለዐቢይ ለግሳለች በማለት የጎሪጥ የምትገላምጣት አቡዳቢም ብትሆን ደንበኛ ገዢ እንጂ አምራች አይደለችም። ለድሮኖች ዜግነት ይሰጣቸው ከተባለ የአብዛኞቹ ዘር የሚመዘዘው ከወደ እስራኤል መሆኑ ነው። ወይም አብዛኞቹ ድሮኖች አይሁዳዊ ናቸው ማለት ይቻላል። አሜሪካ ለድሮኖች ዜግነት በመስጠት በመላው ዓለም ዘራቸውን በማብዛት የጎላውን ስፍራ ትይዛለች።

ለማንኛውም ሕወሓት በጦርነት ውስጥ ስላለች ተዘንግቷት ይሆናል እንጂ ድሮኖችን ከሃይፋ ወደ ደብረ ዘይት በማስመጣት ቀዳሚዋ ተጠቃሽ እራሷ ነበረች። መገጣጠሙ ባይሳካልትም መገጣጠሚያውንም የጠነሰሰችው ራሷው ናት። ከክንፈ ዳኘው መታሰርም በኋላ ስሙን የቀየረው አዲሱ ሜቴክ የድሮኖቹን መገጣጠሚያ እንዳስቀጠለውና እነንደገፋበት ሲነገር ነበር።

ከዚህ በታች ያለው ማስፈንጠሪያ ሱዳን ትሪቡን ኢትዮጵያ ከ7 ዓመታት በፊት የጦር ድሮን ማምረቷን የዘገበበት ነው https://sudantribune.com/spip.php?article45518

Subscribe To Our Newsletter

[mc4wp_form id="318"]