Press "Enter" to skip to content

ትህነግ ውልደቱም ሆነ ዕድገቱ ሴራና ጥፋት ነው – ኮሌኔል ደመቀ ዘውዱ

(ኢ ፕ ድ ዳንሻ ) – ትህነግ ውልደቱም ሆነ ዕድገቱ ሴራና ጥፋት ነው ሲሉ የወልቃይት ጠገዴ ማንነት አስመላሽ ኮሜቴ አባል ኮሌነል ደመቀ ዘውዱ ተናገሩ።ከሀዲው የትህነግ ቡድን በአገር አለኝታ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው አሳፋሪና ወራዳ ተግባር ቡድኑ የአገር ካንሰርና ጠላት መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ገለጹ፡፡

ኮሌኔል ደመቀ ዘውዴ ከሀዲው የህውሀት ቡድን በሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ትህነግ ውልደቱም ሆነ ዕድገቱ ሴራና ጥፋት ነው ። ሁልጊዜም ቢሆን አገርና ህዝብ የለውም ፤ ለእሱ አገርና ህዝብ ጥቅም ብቻ ነው” ብለዋል ።

ለአገርና ለህዝብ የቆመና አሳቢ ቢሆን ኖሮ ለአገር ሉዓላዊነት፣ ለህዝብ ደህንነትና ሰላም መስዋዕት እየሆነ በሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት አይሰነዝርም ነበር ብለዋል፡፡

የትህነግ ዓላማና ህልም የትኛውም ህዝብ አጥፍቶ ቢሆን ገንዘብና ጥቅም ማግኘት ብቻ መሆኑን አመልክተው፤ ይህን ዓላማው ለማሳካትም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶችና ጥቃቶች በማቀድ ሲያስፈጽም እንደነበር አመልክተዋል ።

በተለይም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚኖረው አማሮች ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዲደርስበት ቡድኑ ሌት ተቀን እንደሚሰራ አመልክተው ፤ዓላማውም በአማራ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲነሳ በማድረግ በሚፈጠረው ክፍተት ወደ ስልጣን እመለሳለሁ፣ ያጣሁትንም ጥቅም ተመልሼ አጋብሳለሁ በሚል መነሻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ትህነግ ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት ሲገዛ ፌዴራላዊ መንግስት ይባል እንጂ አሃዳዊ መንግስት ነበር ያሉት ኮሌነሉ፤እሱ የፈለገውን ሀሳብና ዓላማ ብቻ ተግባራዊ ያደረግ ነበር ፤ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የመብት ጥያቄ ሲያነሱ ከማፈን፣ከመግደልና ከማሰቃየት ባለፈም በየክልሎቹ ወኪል አስቀምጦ የአገርንና የህዝብ ገንዘብን ሲዘርፍና ሲበረብር ነበር ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ነቅቶ ዘረፋውንና ኢ ፍትሀዊነትን በጽኑ በመታገሉ ቡድኑ ከስልጣን ተገፍቶ ወደ መቀሌ መሸሹን አውስተው፤ አሁን ያለው የለውጥ መንግስት ችግሮችን በውይይት ለመፍትት ከልክ በላይ ታግሷል ብለዋል ፡፡

ይህ እኩይ ቡድን ውልደቱም ሆነ ዕድገቱ በሴራና በጥፋት በመሆኑ አሁንም ህዝቡ መካከል ግጭት ከመቀስቀስ፣ ከማፋን ፣ከመግደልና ከማሸማቀቅ ባሻገር በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር የእሱን ዓላማና ሀሳብ ለማስፈጸም እየተውተረተረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

“ጦርነት ህይወትን ይበላል፣ንብረትን ያጠፋል አገርን ይጎዳል” ያሉት ኮሌነል ደመቀ፤ ስግብግቡ የትህነግ ቡድን መንግስት ተገዶ ጦርነት ውስጥ እንዲገባ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡

እሳቸው የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሜቴ አባል በመሆናቸው ከእሳቸውና ከቤተሰባቸው ባሻገር በወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ዛቻ፣ማስፈራራት፣ጫና፣ እንግልትና አፈና ያደርስበት እንደነበር አስታውሰው ፤ እኔ በእግዜአብሄር ፈቃድ በአማራ ህዝብ ድጋፍ ከብዙ መከራ ነጻ ወጥቻለሁ ብለዋል፡፡

ዳንሻን ጨምሮ ሌሎች የወልቃይት ጠገዴ አካባቢዎች ነዋሪዎች በመከላከያ ሰራዊትና በአማራ ልዩ ሀይል ከአፋኙና ከአፓርታይድ ቡድን ነጻ በመውጣታቸው ደስታቸውን እየገለጹ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ ለነጻናት እና ለዲሞክራሲ በተደረገው ትግል ውድ ልጆቹን መስዋእት ቢያደርግም በትግሉ ውጤት ግን ተጠቃሚ አለመሆኑን አመልክተው ፣ ህዝቡ በአንድ ለአምስት አደረጃጃትም ታፍኖ መቆየቱን አመልክተዋል።አሁንም ለዚህ ዘራፊ ቡድን መጠቀሚያ መሆን እንደሌለበትና ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ ይህን አፋኝና የራሱን ጥቅም ብቻ የሚያሳድድ ቡድን መታገል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የትግራይ ልዩ ሀይል አባላትና ሚሊሻዎችም ለመከላከያ ሰራዊትና ለአማራ ልዩ ሀይል እጃቸውን መስጠት እንደሚኖርባቸው አመልክተው ፣ ከአማራም ሆነ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር በሰላምና በፍቅር መኖር እንደሚችል አመልክተዋል።

አሁንም እኩይ ቡድኑ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭትን ለመቀስቀስ የቀድሞ የደህንነት አባላት ሽማግሌ፣ የሀይማ ኖት አባት፣የእአምሮ በሽተኛ፣ መነኩሴና አዛውቶች በመምሰል እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል ። ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ ራሱንና አካባቢውን በንቃት መጠበቅ፣ ጸጉረ ልውጥ ሰዎችን ሲያይ እየያዘ ማጣራት እንደሚኖርበት አስታውቀዋል ፡፡

ቡድኑ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በመጠቀምና የራሱን ሀይል በማዘጋጀት የአገር አለኝታ የሆነውን ተቋም ለማፍረስ ሙከራ ማድረጉን ገልጸው፤መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእኩይ ቡድኑ ሰንኮፉ እስኪነቀል ድረስ ከመከላከያ ሰራዊቱና ከመንግስት ጎን በመቆም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

More from ፖለቲካMore posts in ፖለቲካ »

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *