Press "Enter" to skip to content

ዝክረ ጌታቸው ረዳ – ከተማሪው

ጌታቸው ረዳን የማውቀው መቐለ ዩንቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ ነው። ተማሪው ሁሉ በተለይም ሲኒየሮች ስለሱ ጨዋታ አዋቂነት፣ የትምህርት አሰጣጥ ችሎታና እውቀት ያወራሉ። ስለ እንግሉሊዘኛ ጃርገኑ ይወራለታል። የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ሎጅክ እንዲያስተምረን ተመድቧል። ሁላችንም እሱን ለማወቅ ጓጉተናል።

መጣ… ወደ ክፍል ግቡ ተባልን። ክፍሉ ፀጥ ብሏል…ድምፁን ከፍ አድርጎ…ጃ..ያስተሰርያል..እያለ እያንጎራጎረ ገብቶ…በያዘው የሃይላንድ ውሃ ፊቱን ታጠበ። ከእንቅልፉ መንቃቱ ነው መሰለኝ፣ ብቻ እንጃ ያው ፍሬሽ ስትሆን ትደናገጣለህ፣ ሁሉም ነገር እንግዳ ይሆንብሃል። ያኔ በ97 ቴዲ አፍሮ ካሴት አውጥቶ ነበር። ደህና አደራችሁ ሳይለን፣ የቴዲ አዱሱ አልበም እንደተመቸው ነገረን። ከዛም ስለ ሎጅክ፣ አመክንዮና ህፀፅ ዘረገፈብን።

ስለ አንድ ህፀፀ ሲያስረዳ ምሳሌው የመንግስቱ ኃይለማርያም ንግግሮችና የራያን ባህልና ወግ በምሳሌነት እያዋዛ ነበር። እንደውም ትላንት ጦርነቱ ስላለበት ሁናቴ በህፀፅ የተሞላው ማብራሪያው የመንጌን ይመስላል። …”እነሱ አንድ ኮረብታ ሲይዙ የድል ጥማት ስላለባቸው ከፍ አድርገው ያወሩታል፣ ጦርነት በሰዓታት ውስጥ የሚቀያየር ነገር ነው…” በአብነት መግለፅ ይቻላል።

ሲያስተምር የሚያዘጋጀው ኬዝ የወሎ ራያን አማርኛ በመጠቀም ነበር፣ አንድ ጊዜ “ሰታቴ ሙሉ ወጥ ተደፍቶበት” የሚል ሃረግ ተጠቅሞ የአዲስ አባ ልጆች “ሰታቴ” የሚለውን ቃል ዲክሽነሪ ውስጥ በመፈለግ ሰአታቸውን አቃጥለው ነበር ሌላ ጊዜ ደሞ አጎቴ “በነጭ ባህር ዛፍ ሲጎነፍ” ሰራተኛው በአጎዛውና በብርድ ልብሱ አፍናው ከሞት አፋፍ ቢተርፍም ለሌላ በሽታ ተጋለጦ “ሞኝ ባገኝ እና ዋግምት ተበጥቶ” እንደምንም ተረፈ…እያለ ያወዛግብ ነበር።

መቼስ አያልቅበት፣ አንዴ ደግሞ “እኛ ቤት ሽንት ቤቱ አጠገብ ያለው ቧንቧ ፈንድቶ “ፀበል ፈለቀ” ተብሎ፣ ተባረከና የመንደሩ ህሙማን መጠጣት ጀመሩ ከዛም ቅዘን ለቀቀባቸው የሰፈሩ ሰውም ጉድ..ጉድ..ህመሙን ” ጎለጎለው” ማለት ጀመሩ ነገር ግን ውሃው ከሽንት ቤቱ ጋር ግንኙነት ስለነበረው ለሌላ በሽታ ተጋልጠው ኑሯል፣ ሥለዚህ አባበይ ከውል ውጭ ሃላፊነት ሊጠይቅ ይችላል? ይላል፣ ተመቼኝ። ሌሎች ግን መረዳት ይከብዳቸው ነበር።

እናማ! ይላል የኛ ሰው ታሪኩ ከቆመበት ሲቀጥል። ጌች በሴሜስተር ቢበዛ ሦስት ክፍል ጊዜ ቢያስምር ነው፣ በእጅ ፅሁፍ ክላስ እንዳለ ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ይለጥፋል የሰማ ላልሰማ አሳውቆ ክፍል ውስጥ እንከትማለን ከዛም “ደቡብ አፍሪካ ለስራ ሄጄ ስለነበር አልተመቸኝም ነበር ይላል” እውነታው ግን አቦይ ስብሃት ጋር እየቃመና ውስኪውን እየኮመኮመ ብልግናውንም ፓለቲካውንም እያጫወተ ስለሚከርም ነበር። የት ሄደ ብሎ ጠያቂ የለውም፣ ለምን እንኳን ቢባል የትምህርት ቤቱን ዲን “እራሴ ፈትኘ ቀጥሬ”..እያለ በኛ ፊት ያሾፍበት ነበር።

ወደ ፓለቲካ..

ወቅቱ የ97 ምርጫ ስለነበር የመቀሌ ዩንቨርስቲ የህግ መምህር እየተባለ “በቪኦኤም፣ በዶቼቬሌም” ስለ ምርጫው ሃሳቡን ማካፈል ጀመረ፣ በትግራይ በተለይም በመቐለ ስሙ ገነነ። ጠላ ቤት፣ አረቄ ቤት ብትገባ ስለጌች ይወራል፤ ስለጅዝብናውና ጉብዝናው። ነገር ግን በዚህ መንገድ በዩንቨርስቲው መቀጠል አልቻለም፣ ዶክተር ጌታሁን (ከምርጫ ቦርድ የቦርድ አባልነት ራሱን ያገለው) የጓደኝነት ምክሩንና ቅሬታውንም ጭምር ገልፆ ማስጠንቀቂያ አውጥቶ ስላልተስተካከለ የሥራ ስንብት ማስታወቂያ አወጣበት። በወጣበት ጠፋ። ከዚያም አዲስ አባ ገብቶ በታዋቂዋ “አዲስ ነገር” ጋዜጣ አምደኛ በመሆን የኢሕአዴግን ፓሊሲ በመደገፍ መፃፍ ጀመረ።

የቴዲ አፍሮ ክስ፣

ያኔ ፍሬሽ እያልን በቴዲ የሙዚቃ ፍቅር ወድቆ “ጃ ያስተሰርያል” ሲጨፍር የነበረው ሰውየ የቴዲ አፍሮን “ተክለ ስብእና” የሚያኮስስ፣ ቴዲ አይከን ሳይሆን ተራ ዘፋኝና ነብስ ገዳይ መሆኑን የሚያትት መልእክት ያለው ትንታኔ በአዲስ ነገር ጋዜጣ አወጣ። በመለስም አመኔታና መወደድን አተረፈ፣ ካድሬው ሁሉ እሱ የሚፅፋቸውን አሳደው ማንበብ ጀመሩ፣ የአዲስ ነገርም ገበያ ደራ ምንም እንኳ መጨረሻዋ ቢያሳዝንም። በተቃራኒው እኛም ይህ ሰውየ ወዴት እየሄደ ነው ማለት ጀመርን።

በቃ ወጉት!

ከዛም አጅሬ በመሰላሉ በፍጥነት መውጣት ጀመረ። የወጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ፣ የሕውሃት መአከላዊ ኮሚቴ፣ ሥራ አስፈፃሚ እያለ…አፈ ንጉስ ሆኖ አረፈው። በዚህ ሂደት ውስጥ ከስሪቱ፣ ካስተዳደጉ ወይም ከልቦና ውቅሩና ስብዕናው ጋር እየተጋጨ ከትህነግ ጋር አብሮ በደህና ጊዜ የተካናትን አምክንዩ እየመነዘረ ኢትዮጵያን ወደ አፋፍ ገፋት።
ይህን ነገር ያነሳሁት ዝም ብየ አይደለም ትህነግ ምን ያህል “ኢትዮጵያዊ የማንነት ሥነ ልቦናህን ሰልባ በጠባብ ብሄርተኝነት አስክራ እንደፈለገች ሎሌ ልታደርግህ እንደምትችል” ለማሳየት ነው።

ከጊዜ ወደ ጊዜ የመንፈስ እረፍት ስለሌለው ፊቱ ሁሉ በማድያት ፀለመ፣ ሂድ ተናገር እያሉ ከኢትዮጵያዊ ስነ ምግባር ባፈነገጠ መልኩ ከማቀራረብ ይልቅ የሚያራርቁ፣ ከትብብር ይልቅ መናናቅን ያነገቡ ስድቦችን በሃገሩና በመሪዎቹ ያዘንብ ጀመር። ስለ “ሃበሻ ጀብዱ ሲተርክ” የነበረው ሰውየ የጋራ ታሪክ የለንም ማለት ጀመረ። የዲጅታል ወያነ ግሪሳም ሰኒታይዘር እያሉ ጅግንነቱን ነገሩት፣ አሰከሩት። ቅሉ ግን በኢትዮጵያዊነቱ ከማይደራደረው የራያ ህዝብ ጋር እየነጠሉት ነበር። ትላንት በቴሊቪዥን እየተንተባተበ ተናግሮ አንገቱን ሲደፋ ያኔ ፍሬሽ እያለን ስለኢትዮጵያዊነት ሲያወራን የነበረው ሁሉ ትዝ አለኝ፣ አዘንኩለት።

ወንድሜን ሰለቡት፣ ትህነግ ነብስሽ ያይጥ ይሁን!

Dr Fikru Yimer

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *