Press "Enter" to skip to content

”ቀኑን ሙሉ ሳለቅስ እና ስጸልይ ነው የምውለው” (የአቶ ልደቱ አያሌው እናት)

ዛሬ ቅዳሜ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ከ40 ደቂቃ ላይ ስልኬ ለስድስተኛ ጊዜ የጥሪ ድምፅ አሰማ፡፡ ስራ ቦታ ላይ ስለነበርኩ ትንሽ ዘግይቼ ከኪሴ ውስጥ ስልኬን አወጣሁ፡፡ ደዋዩን ሳየው የአቶ ልደቱ ወላጅ እናት ናችወ፡፡ ከሰሞኑ አይቻቸው ስለማላውቅ ምን ሆነው ነው የጠፉት እያልኩ ሳስባቸው ነበር፡፡ እኔ ስልካቸው ቢኖረኝም ምን አዲስ ነገር ይዤ ነው የምደውልላቸው? ብደውልስ እናትን የማፅናናበት፤ የማበረታበት ቃል ከወዴት አባቴ ላገኝ ነው? ብዬ ስለምሳቀቅ ነው ሳልደውል የቆየሁት እና ትንሽ ፀፀት ቆንጠጥ አደረገኝ፡፡

ግን እሳቸውም የልጃቸው ጉዳይ አያስችላቸውም እና ለወትሮው ቶሎ ቶሎ ይደውሉ ስለነበረ ምን ሆነው ይሆን የጠፉት ብዬ ሳስባቸው ስለነበረ አሁን ምን ልላቸው ነው? በምንስ ቋንቋ ነው የማፅናናቸው እያልኩ በመሳቀቅ ስልኩን አነሳሁ እና

” ሃሎ“ እልኩኝ
“ልጄ እንዴት ነህ” አሉኝ
” ማዘር እንዴት ነዎት? ሰላም ነው? ጤናዎት እንዴት ነው? ምነው ጠፉ?“ ብዬ መረበሼን በሚያሳብቅ ሁኔታ ጥያቄዬን አዥጎደጎድኩት፡፡
“ ልጄ ሰላም ነኝ አንተ እንዴት ነህ? ” አሉኝ ድክም ባለ ድምፅ
” ሰላም ነኝ ማዘር ያው የማልደውለው ምንም አዲስ ነገር ስለሌለ እየተሳቀቅኩ ነው፡፡ እርስዎም ምነው ጠፉ? እንደ ድሮስ ችሎት ምነው አይቼዎት አላውቅም“ አልኳቸው፡፡

“ አዬ ልጄ ምን ደህንነት አለ ብለህ ነው፡፡ መሽቶ እስኪነጋ ልጄን በህይወት አገኘሁ ይሆን? እያልኩ ስገላበጥ ነው የማድረው፡፡ መሽቶ ሲነጋ በህይወት የማገኘው አይመስለኝም፡፡ ቀኑን ሳለቅስ ስፀልይ ነው የምውለው፡፡ በዚህ የተነሳ ሰውነቴ ትንሽ ስለቀነሰ ሲያየኝ እንዳይሳቀቅ ብዬ ነው የማልመጣው” አሉኝ ሳግ እየተናነቃቸው፡፡
”ማዘር ጠንከር ነው ማለት ያለብን፡፡ እግዚአብሄርን ተስፋ ማድረግ ነው፡፡ ልደቱም ቢሆን ጠንካራ ነው አይዞዎት“ አልኩ ለማፅናናት ከረዳ ብዬ

“አይ ልጄ እንዴት ብዬ ልጠንክር ልጄ ከበሽታው ጋር እየታገለ ጠባብ እስር ቤት ውስጥ ተዘግቶበት፡፡ እኔማ ቀንም ለሊትም እየጸለይኩ ነው፡፡ ደሞ ልጄ ልደቱ እኮ ሰው ነው፡፡ ከብረት አልተሰራ፡፡ ስቃዩን ህመሙን ለሰው ስለማይናገር ነው፡፡ ተጨንቆ የተጨነቁትን የማፅናናት፣ ታሞ መታመሙን ሰው እንዲያውቅበት፣ በሱ ምክንያት ሰው እንዳይቸገርበት ስለሚፈልግ ነው እንጂ ልጄ በጠና ነው የታመመው ” አሉኝ ሳግ እና ለቅሶው ድምፃቸውን እየቆራረጠው፡፡ አንጀቴ ተላወሰ፡፡ ጮሆ ማልቀስ ለመጀመሪያ ግዜ አማረኝ፡፡

እንደምንም እራሴን ተቆጣጥሬ
” ማዘር ያለበትን ሁኔታ ለመንግስት፣ ለመገናኛ ብዙሃን እና ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ለማሳወቅ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ የግል ዶ/ሩንም የተማፅኖ ደብዳቤ ይፋ አድርገናል፡፡ ስለዚህ ቢያንስ ቢያንስ በዋስ ተፍትቶ ህክምና የሚያገኝበትን ሁኔታ ይኖራል ብለን ተስፋ አድርገናል፡፡“ አልኳቸው ምን አልባት ህመማቸውን ስቃያቸውን ያቀለልኩ መስሎኝ ነገር ግን የልደቱ እናት የዋዛ አይደሉም

“ ልጄ የናንተን ጥረት እና ጩኸት እየተከታተልኩ ነው፡፡ ግን እናንተ ስለበሽታው የምትናገሩትን ፖለቲካ ነው ያደረጉት፡፡ ማስረጃውንም የተጭበረበረ ማስረጃ ነው የመሰላቸው፡፡ ምን አለበት ልጄን በዋስ ለቀውት ህክምናውን እንዲከታተል ቢያደርጉት፡፡ ልደቱ እንኳን በዋስ ተለቅቆ ከፍርድ ቤት ሊቀር ሞት ተፈርዶብሃል ና ቢባል የሚመጣ ነው፡፡ ችግሩ ግን ህመሙን እና ስቃዩን የሚረዳለት ወገን ነው ያጣው፡፡ ህመሙን ስቃዩን ፖለቲካ አደረጉት፡፡ ልጄ ህመሙን ሳያስታምም አይኔ እያየ ምንም ሳላደርግለት ሊሞትብኝ ነው እባክህን ልጄ ” እምመልሰው ነገር ጠፋኝ፡፡ ፀፀት እና ምንም ያለማድረግ ባዶነት ውስጤን ሲቧጥጠኝ ተሰማኝ፡፡ መልስ ያልመለስኩበት ሰከንድ የዓመት ያህል የረዘመ መሰለኝ፡፡ ማዘርም ዝምታዬን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ ጮኸው ማልቀስ እስኪቀራቸው ሳግና ሲቃቸውን በስልኩ አደመጥኩ፡፡ ማፅናኛ ቃል አጣሁ፡፡ ዝምታ ዋጠኝ

” ልጀ ሁሉም እናት አለው፡፡ መንግስትም፣ ጋዜጠኞችም እነዚህ ሰብዓዊ ኮሚሽን ያልካቸውም እኔ ልለምናቸው፡፡ የልጄን ስቃይ ላስረዳቸው፡፡ ህመሙን ልንገራቸው፡፡ የእውነት መታመሙንም እያለቀስኩ ልንገራቸው፡፡ እባክህን አንተን የሚያገኙት ጋዜጠኞች እኔንም ያግኙኝ፡፡ እናንተን አላመኑአችሁም፡፡ እኔን ሊያምኑኝ ይችላሉ፡፡ እባክህን እባክህን ልጄ“ አሉኝ፡፡
“ እሺ” አልኳቸው ከስቃይ እና ከሰቀቀን የምድን መስሎኝ በመቻኮል፡፡ ግን አንድ ያሉት ነገር ጭንቅላቴ ውስጥ ደጋግሞ ደጋግሞ ደወለ፡፡
” ልጄ ሁሉም እናት አለው“
እውነት ግን ሁሉም እናት አለው?
የነገ ሰው ይበለን!

ጥቅምት 21/2013 ዓ/ም
አዲስ አበባ
======
ምንጭ የፓርቲው ሊቀመንበር አዳነ ታደሰ

More from ፖለቲካMore posts in ፖለቲካ »

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *