Press "Enter" to skip to content

እነአቶ እስክንድር ነጋ የፀረ ሽብር አዋጅን በመተላለፍ ክስ ተመሰረተባቸው፣ 139 ገጽ የክስ ፋይል ተሰጣቸው

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፕሬዚደንት አቶ እስክንድር ነጋ ላይ አቃቤ ሕግ የፀረ ሽብር አዋጅን በመተላለፍ ክስ ሁለት ክስ መመስረቱን ጠበቃቸው አቶ ሔኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ገለፁ። በፖለቲከኛውና ጋዜጠኛው በአቶ አስክንድር ላይ የቀረቡት ክሶች ኃይልን በመጠቀም መንግሥትን ለመቆጣጠር የተደረገ ሙከራን የሚጠቅሱ መሆናቸው ተመልክቷል።

ዛሬ ጠዋት አቶ እስክንድር ነጋ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ አለማወቃቸውንና አካልን ነፃ ለማውጣት በከፈቱት የክስ መዝገብ ለከሰዓት ቀጠሮ ስለነበራቸው እርሱን ሲከታተሉ እንደነበር የተናገሩት አቶ ሔኖክ፤ ደንበኛቸው ያለጠበቃ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ተናግረዋል። በኋላ ላይ ባገኙት መረጃም ፍርድ ቤት ቀርበው የክስ መዝገብ እንደተሰጣቸው ማወቅ ችያለሁ ብለዋል።

አቶ ሔኖክ እንደተናገሩት በአቶ እስክንድር ላይ መደበኛ የወንጀል ሕግ መሰረት በማድረግ ዋና ወንጀል አድራጊ ሆነው “የጦር መሳሪያን በመጠቀም የመንግሥትን ሥልጣን ለመቆጣጠር አመፅ በመፍጠር” እና “የፖለቲካ ዓላማን ለማራመድ በመስማማትና ሕዝብ በማሳመጽ የሽብር ተግባር በመፈፀም መንግሥትን በኃይል ለመቆጣጠር” የሚሉ ክሶች ተመስርተውባቸዋል ብለዋል።

በክስ መዝገቡ ላይ የተከሰሱት ሰባት ሰዎች ሲሆን አራቱ የባልደራስ ከፍተኛ አመራሮችም መሆናቸውን ጠበቃው ለቢቢሲ ገልጸዋል። በአቶ አስክንድር ላይ ሁለቱም ክሶች የቀረቡባቸው ሲሆን በሌሎቹ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ላይ ግን የተመሰረተው አንድ ክስ ብቻ ነው። በመዝገቡ ላይ ሌሎች ሦስት ሰዎች ያሉ ሲሆን በአካል ያልተገኙ ወይም በፖሊስ እጅ የሌሉ ሁለት ሰዎች ክሱ ውስጥ እንደተካተቱ አቶ ሔኖክ ተናግረዋል።

አቶ እስክንድር ከዚህ ቀደም “ጠበቃዬን አሰናብቻለሁ” ማለታቸውን ያነሳንላቸው ጠበቃ ሔኖክ፤ ይህን ያሉት የቅድመ ምርመራ ፋይል በነበረበት ጊዜና በአንድ ጉዳይ ላይ ብቻ ማለታቸውን በመጥቀስ፤ ለአቶ እስክንድር አካልን ነፃ የማውጣት የከፈቱት ክስ ላይ እርሳቸውን ወክለው መቅረባቸውን ተናግረዋል። በሌሎች የፍትአብሔር ጉዳዮችም እርሳቸውን ወክለው እየተከታተሉ እንደሆነም አክለዋል።

“በሌላ ወንጀል አዲስ ክስ ሲቀርብባቸው ከዚህ በፊት በነበረ መዝገብ ላይ “ጠበቃ አልፈልግም” ብለሃል፤ የሚያስብል የሕግ መሰረት የለም” ብለዋል። በመሆኑም አቶ እስክንድር በዚህ መዝገብ ላይ ጠበቃ አልፈልግም ብለው ለፍርድ ቤቱ እስካልተናገሩ ድረስ፤ ፍርድ ቤቱ ጠበቃ የሚያገኙበትን መንገድ ሊያግዛቸው ይገባልም ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በአቶ እስክንድር ላይ ቀዳሚ ምርመራ ምስክሮች ተሰምቶ ካለቀ በኋላ አቃቤ ሕግ በ15 ቀን ውስጥ ክስ ይመስርት ተብሎ ክስ ሳይመሰርት 15 ቀን በማለፉ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

ፍርድ ቤቱም የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ [ሐሙስ] ከሰዓት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ጠዋት ላይ ክስ ተመስርቶባቸዋል። በመሆኑም የአቶ እስክንድር ነፃ መውጣት በቀዳሚ ምርመራ በፍርድ ቤት የተሰጠውን ትዕዛዝ መሰረት አድርጎ በተቀመጠው አካልን ነፃ የማውጣት መዝገብ ላይ የሚወሰን ሳይሆን አሁን በቀረበባቸው ክስ ነው ብለዋል አቶ ሔኖክ።

አቶ ሔኖክ “ቀደም ሲል የነበረው የፀረ ሽብር አዋጁ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸውን ወገኖች ለማጥቃት ነበር ይጠቀሙበት የነበረው፤ አቶ እስክንድር እንደ ማንኛውም ሰው የሚጠረጠሩበት እድል ቢኖርም እንኳን የሽብር ተግባር ፈፅመዋል ብዬ አላምንም” ብለዋል።

ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም፤ በቀዳሚ ምርመራ የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡም ጭምር የሚያስከስሳቸው የረባ ማስረጃ አለመኖሩን ጠቅሰው፤ “አሁን ባለው ሁኔታ ላይ የፀረ ሽብር ሕጉ የተለየ አመለካከት ያላቸውን ዜጎች ለማጥቃት የቀረበ ነው፤ ትናንት ስንፈራ የነበረው ተመልሶ እንዳይመጣ ስጋት አለኝ” ብለዋል።

የሽብር ሕጉም እንደ ከዚህ ቀደሙ ዜጎችን ለማሸማቀቂያ፤ፓርቲዎችን ለማክሰሚያ እንዳይውል ስጋት እንዳላቸውም ጠበቃ ሔኖክ ለቢቢሲ ተናግረዋል።አቶ እስክንድር ነጋ በሚቀጥለው ሐሙስ መስከረም 8/2013 ዓ.ም ቀጠሮ እንደተሰጣቸውም ነግረውናል።

አቶ አስክንድር ነጋ የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደልን ተከትሎ ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ ሲሆኑ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ በአስር ላይ ከሁለት ወራት በላይ ቆይተዋል። ቢቢሲ

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *