Press "Enter" to skip to content

“የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ አሁን ላይ ፀጥ እንዳለ ባህር ሆኗል” – አቶ አንዷለም አራጌ

የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ አሁን ላይ ፀጥ እንዳለ ባህር ይምሰል እንጂ በሀገሪቱ ያለው እውነታ ኢትዮጵያዊነት ጠፍቷል። የኢዜማ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አንዷለም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ አሁን ላይ ፀጥ እንዳለ ባህርና ዝም ብሎ እንደሚፈስ ውሃ ጎልቶ አይሰማም።በሌላ በኩል ደግሞ ጥቂቶች እንደሚረብሽ ሞተር ድምፅ እያሰሙ በባህሩ ላይ የሚሄዱ ጀልባዎችን መስለው በመታየት ጩኸታቸው የኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ የአንድነት መንፈስ የሌለ አስመስሎታል።

ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት በየአካባቢው የሚታየው ብሄር ተኮር ግጭት በአገሪቱ አገራዊ አንድን የአገር ፍቅር ስሜት የጠፉ ቢያስመስሉትም ህዝቡ ጉዳቱ የከፋ እንዳይሆን ያደረገው ሁለንተናዊ ጥረት ተቻችሎ የመኖርና ኢትዮጵያዊነት ዛሬም በሁሉም ዜጋ ልብ መኖሩን ያመላከተ መሆኑን አስታውቀዋል ።

ለዚህ ደግሞ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ የነበረው ችግርና ህዝቡ ያደረገው ትብብር አብነት ተደርጎ ሊጠቀስ እንደሚችል ተናግረዋል።«ኦሮሚያ ላይ አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ችግሩን ያቆመው ህዝቡ ነው።ህዝቡን ያቆመው የባጀ፤ የኖረ የኢትዮጵያዊነት ስሜት፤ ተቻችሎ የመኖር እሴቱና ሃይማኖታዊ መርሁ ነው» ብለዋል። ፅንፈኞቹ የሌላ ብሄረሰብ ተወላጆችን በመከታተል ጥቃት ሲያደርሱ ህዝቡ በጉያው በመሸሸግ ለመከላከል ጥረት ማድረጉን አመልክተዋል።

እንደአቶ አንዷለም ገለፃ፤ 1997ዓ.ም ኢትዮጵያዊነት ሞተ ሲባል አገሩን ሞልቶ የቆመው አስቀድሞም ህዝቡ ውስጥ ስሜቱ ስለነበረ ነው።በተጨማሪም እነዶክተር አብይ ሲመረጡ «ሆ» በማለት የወጣው ይህ ህዝብ ስሜት አስቀድሞም በውስጡ ስለነበር ነው።በመሆኑም በአገሪቱ ኢትዮጵያዊነት ጠፍቷል፤ ዘረኝነት ነግሷል የሚባልበት ደረጃ አለመሆኑን ያሳያል፡፡

በአንዳንድ ሰዎች የብሄርተኝነት አስተሳሰብ ጫፍ ደርሷል በሚባልበት በትግራይ ክልል እንኳ ህዝቡ ለአገሩ ያለውን ፍቅር የሚያሳይበትን እድል ባለማግኘቱ እንጂ ሁኔታዎች ቢመቻቹለትና ነፃነቱ ቢጠበቅለት እንዲህ የሚሉትን አካላት እንደሚያሳፍራቸው ያላቸውን እምነት ምክትል ሊቀመንበሩ ገልፀዋል።«ኢትዮጵያዊነቱ ጎልቶ ሲወጣ ለኢትዮጵያዊነት ክብር ሲቆም እናየዋለን።ዛሬ ግን ሕወሓት ስለሚጨፍርና ስለብሄር ብቻ ስለሚያወራ የትግራይ ህዝብ አንደበት ተደርጎ ሊወሰድ አይቻልም» ብለዋል።

እኛ ብናምንበትም፤ ባናምንበትም ህገመንግስቱን ያወጣው ህውሀት ራሱ ነው፤ ሲመራበት ነበር።እሱን አላከበራችሁም እየተባልን ብዙ በደል ደርሶብናል።አሁን ግን መልሶ ራሱ የወለደውን ልጅ ራሱ እየገደለ ነው።ይህ ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል ፡፡

“ የትግራይ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ደም የሚያቃባ ነገር ሰራዊት አዘጋጅቶ ማስፈራሪያና ዛቻ ማድረግ አይጠበቅበትም። የሚያሳዝነው ነገር አንዱም የሕወሓት ባለስልጣን ሄዶ አለመሞቱ ነው።በተመሳሳይ የብልፅግና አመራር ሄዶ አይሞትም።የሚሞተው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው።የሚጋደሉት የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው።ይህንን ግፊት እያደረገ ያለው ደግሞ በዋናነት ሕወሓት ነው”ብለዋል ።

ህውሀት እንደሌሎቻችን ታግሶ መጠበቅ ሲኖርበት በተለየ መንገድ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ለመምሰል ሲል ህዝብ ለማጫረስ ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተው፤ እድሉ በነበረው ጊዜ ዲሞክራሲ በአገሪቱ ማስፈን ሳይችል አሁን ላይ ይህን ለማድረግ መሞከሩ የሚያስተዛዝብ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከብልፅግና ሰዎች ጋር በተጋባው አልህ ምክንያት እንዲህ አይነት የተዛባ ነገር መስራት ትክክል ስለመሆኑ ምንም ጥያቄ የለውም ያሉት አቶ አንዷለም ፣ በመንግስት በኩል ባልተገደበ ሁኔታ ነገሩን ዝም ብሎ መተው ትክክል እንዳልሆነ አመልክተዋል። ከፉከራው፣ ከዛቻው አልፎ ከመጋረጃ በስተጀርባ ትላልቅ ስራዎች መስራት እንደሚጠበቅበትም አስታውቀዋል ፡፡

በእርግጥ ይህንን ዘመን የሚመጥኑ ከሆነ፣ ለኢትዮጵያ ታላላቅ ሰዎች እንሆናለን ብለው የሚያስቡ ከሆነ ቁጭ ብለው መነጋገር ይጠበቅባቸዋል፡፡አባቶቻችንም በዚህ መንገድ ነው ያለፉት።ከብዙ ደም መፋሰስና ፍጥጫ መሃል አንዱ ሌላውን ይቅር ብሎ የኖሩበት ዘመን አለም ብለዋል ፡፡ አዲስ ዘመን

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *