Press "Enter" to skip to content

IQ Test እና የስነ ልቦና ጦርነት

ሰሞኑን አንድ ድርጅት የሐገራትን የማሰብ አቅም ለክቼ እናንተ ኢትዮጵያውያን ከአለም ጋር ስትነጻጸሩ እንደ ህዝብ ማሰብ ይሳናቹሃል አለን።አገኛችሁት ያለንም አማካይ 69 ነው።በነገራችን ላይ በIQ የደረጃ አፈታት መሰረት በአማካይ 69 ማለት የተወሰነ የአእምሮ ችግር ያለበት (Mentally Retarded)እንደ ማለት ነው።ይሄንን ዜና ብዙ የሐገራችን ሚዲያዎች ሳይቀሩ እንደወረደ ሲያስተጋቡት አይቼ ”ከሰደበኝ ስድቤን የነገረኝ”የሚለውን የሀገሬን ብሂል አስታወሰኝ። እንዲህ አይነት ፍረጃዎች በሐገር ላይ ያላቸው የስነ ልቦና ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ስለ IQ በጣም ጥቂት ነገር ልላቹ ወደደኩ።

የማሰብን አቅም የሚለካውን ሙከራ (INTELLIGENCE QUOTIENT) ለመጀመሪያ ጊዜ Alfred Binet እና የስራ ባልደረባው Theodore Simon በ 1905 አዘጋጁት።ሙከራው በዋናነት

ቃላዊና የሆኑና ያልሆኑ ነገሮችን መረዳት (verbal and Non verbal Comprhension) የተለያዩ ቅርጾችን መረዳት(Perceptual Reasoning) መረጃዎችን የማገናዘብ ፍጥነት(processing Speed)

የማስታወስ ብቃትን (Working Memory) የሚመዝን ነው። ይሄ ሙከራ የተዘጋጀበት ዋናው ምክንያት ከእድሜና የክፍል ጓደኞቻቸው ጋር ሲነጻጸሩ የመማር እክል(learning Disabilities) ያለባቸውን ለመለየትና ለማገዝ ነው።

ከአንድ እናት ተገኝተው አንድ ቤት እየኖሩ የተለያየ ብቃት ያላቸውን ሰዎች በምናይበት ዘመን ላይ እንዲህ አይነት ሙከራዎችን ሀገርን ለመፈረጅ ጥቅም ላይ መዋሉ ትልቅ ችግር ያለበት እንደሆነ አምናለሁ።ችግሩን ለማሳየት መጠየቅ ካለባቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች ውስጥ የተወሰኑትን ልጥቀስ

1.ማነው የወከለን?(Sampling Error) ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊየን በላይ ዜጎች የሚኖሩባት ሐገር ነች።እንዲህ አይነት ጥናት ሲሰራ ኢትዮጵያውያንን የወከሉት ሰዎች እነማን ናቸው?የትና ምን ተማሩ?በምን አይነት የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ናቸው?ከከተማ ወይስ ከገጠር ተመረጡ?
የተሻለ የትምህርት እድል ያገኙና ያለገኙ እኩል ሊነጻጸሩ ይገባል?ተነጻጽረው ልዩነት ቢመጣስ ልዩነቱን የፈጠረው ያገኙት የትምህርት እድል ነው እንጂ እንዴት የማሰብ አቅም ነው ይባላል?

2.ባህል ከግንዛቤ ውስጥ ገብቷል?(Cultural Factors)ሙከራው በየትኛውም ባህል ውስጥ የሚሰራ(Culture-Fair) እንደሆነ ይናገሩለት እንጂ እውነታው እንደዛ አይደለም።ለምሳሌ ብዙውን ጊዜ ከሚጠቀሙበት ሙከራ አይነት ውስጥ የተለያዩ ምስሎችን መረዳትና መገጣጠም ሲሆን አሜሪካ ውስጥ ያለ ልጅና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ልጅ ስለ ተለያዩ ቅርጾች አንድ አይነት ግንዛቤ ሊኖራቸው አይችልም።አንድ ምሳሌ ልጨምርላቹ።በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖር አንድ ሰው በአውሮፓ ከሚኖረው ሰው የተሻለ ስለ እጽዋትና የባህል መድሃኒት የተሻለ እውቀት አለው።ብዙውን ጊዜ መመዘኛዎቹ ግን ከምእራቡ አለም የሚነሱ(ethno centric) ናቸው።ጥያቄዎቹ ወካይ አይደሉም።

3.ማን ከማን ተነጻጸረ?(Socio Economic Factors) በጥሩ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለና መብላት ጥያቄው የሆነበት ልጅ እኩል የማሰብ ብቃት የላቸውም።ልዩነቱን የፈጠረው ተፈጥሯዊ የማሰብ አቅማቸው ሳይሆን የኑሯቸው ሁኔታ ነው።

4.ቋንቋ(Language) ብዙውን ጊዜ እንዲህ አይነት ሙከራዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚዘጋጁ ናቸው።ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ሰዎች በእናት ቋንቋቸው ቢጠቀሙ የበለጠ የማሰብ አቅማቻው ይጨምራል።የተሰጠው ሙከራ በምን አይነት ቋንቋ የተሰጠና ሙከራውን የወሰዱት ሰዎችስ የመረዳት አቅምቸው ምን ያህል ነበር?

በሐገር ደረጃ የሚሰጠውን ፍረጃ የተሳሳተ እንደሆነ ብዙ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል።እንዲህ አይነቱ ፍረጃ ህዝባችን ማሰብ አልችልም ችግር አለብኝ ብሎ እንዲያምን ታዳጊዎችም አለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን እንዳይችሉና የበታችነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል።እኛም ሆንን ሚዲያዎቻችን ከመዘገባቸው በፊት ማመዛዘንን ብንለምድ ጥሩ ነው።

እንዲህ እንመን እናሳምን “ፈጣሪ ለሁሉም የሰው ልጅ አንድ አይነት ጭንቅላት ሰጥቷል።እኛ ኢትዮጵያውያን ከማንም ያነሰ ተፈጥሯዊ የሆነ የማሰብ ችግር የለብንም።በአለም አቀፍ ድርጅቶችና መድረኮች ላይ ድንቅ ነገር ሰርተው እድሉን ስናገኝ ከማንም የማናንስና እምቅ ችሎታ ያለን መሆናችንን ያስመሰከሩ ኢትዮጵያውያን ምስክር ናቸው”።

የስነ ልቦናው ጦርነት እንዴት እየተካሄደ እንዳለ የበለጠ ለመረዳት ለምትፈልጉ ከታች ያስቀመጥኩት ጽሁፍ ጠቃሚ ነው። ኤርሚያስ ኪሮስ(ካውንስሊንግ ሳይኮሎጂስት) Jelte M. Wicherts, Conor V. Dolana, and Han L.J. van der Maas, A systematic literature review of the average IQ of sub-Saharan Africans, Intelligence, Volume 38, Issue 1, January–February 2010, pp. 1–20
(ኤርሚያስ ኪሮስ)

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *