Press "Enter" to skip to content

ዳገት ላይ ሰው ጠፋ

ፕራይም ሚዲያ የተባለ የዩትዩብ ቻናል ላይ በእንግድነት የቀረቡት የክብር ዶ/ር አሊ ቢራ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ባለው የሀገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁናቴ ላይ ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል። ለጊዜው በግሌ ባላረጋገጥኩትና የብልጽግና ፓርቲ ሚዲያ ነው በተባለው በዚሁ ቻናል ላይ “ከአርቲስቱ ሞት በኋላ በኦሮሚያ ክልል የተካሄዱትን ግድያዎችና የንብረት ውድመቶች እንዴት ትመለከተ ዋለህ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው የሰጡት ምላሽ እጅግ አስደንጋጭና በማናቸውም መስፈርያዎች ህጋዊነት የሌላቸው የጥላቻ መልዕክት እንደሆኑ ቋንቋውን የሚሰማ ማንም ሰው ሊገነዘበው የሚችል ነው።

አሊ ቢራ ለዚህ ጥያቄ ሲመልሱ “ሀጫሉን የመሰለ ታላቅ አርቲስት ያጣ ህዝብ ከዚህ በላይ ሊያደርግ ይችል ነበር” በማለት ድርጊቱን የማንኛ ውም የሰው ልጅ ባህሪና አለማቀፋዊ እውነታ ለማስመሰልም “ህዝቡ ለተፈጸመው ሁኔታ ሪአክት ነው ያደረገው” ሲሉ መልሰዋል።

አርቲስቱ አክለውም “ከኦሮሞ ህዝብ ቁጥር አንጻርም ይህን ድርጊት የፈጸሙት አካላት በቁጥር እዚህ ግባ የማይባሉ ጥቂት ናቸው” በማለት “ሀጫሉ ተገድሎ ኦሮሞ ዝም የሚል ከሆነ ራሱ እንደሞተ እቆጥረዋለሁ” ብለው ብሄርና ሀይማኖታቸው ብቻ እየተለየ ለተገደሉ 300 ንጹሀን ዜጎች ህይወት “የአጸፋ ምላሽ ነው” አይነት ማብራርያ ሰጥተዋል።

ይህ እንዴት “ሪአክት” (ግብረ-መልስ) ሊባል ይችላል? ሀጫሉን ማን ገደለውና ማን ላይ ነው ሪአክት የሚደረገው? እንዴት በምንም ጉዳይ ውስጥ የሌሉና ተራ ኑሮ ኗሪዎች ለሀጫሉ ግድያ ግብረ መልስ ተወስዶ ይገደላሉ? እያልን በአመክንዮ ለመሞገት አይቃጣንም። በፍጹም!

“ልክ ሌባ ሞባይል ሊሰርቅህ ኪስህ ሲገባ በድንጋጤ የምትወስደው አይነት እርምጃ ነው” ሲሉም የተፈጸመው ጅምላ ግድያ “ተፈጥሯዊ” ነው በማለት “በቀላሉ እዩት” ምክራቸውን በየትኛውም ቋንቋና አመክኒዮ ልንከራከራቸው አናስብም!

አሊ ቢራ ከወራት በፊት በአሜሪካ ሀገር በፖሊስ ተገድሎ የጥቁር አሜሪካውያንን የእኩልነት ጥያቄ ለማስነሳት ምክኒያት የሆነውን ጆርጅ ፍሎይድን እንደምሳሌ በመጥቀስ – በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረውም እንደዝያው አይነት ነው ሲል አስረድቷል። ይሁን እንጂ በምን አይነት መንገድ ይህ ከ300 ንጹሀን ግድያ ያውም ከብሄርና ከሀይማኖት ለይቶ ግድያ ጋር እንደሚገናኝ እንዲያብራራልንም አንጠብቅም!

የአርቲስቱ አነጋገር በአጭር ቃል በሀገሪቱ ህግም፣ በሀይማኖት አስተሳሰብም፣ በሞራል ደረጃና በተለይ እድሜውን ሙሉ ለማህበረሰብ ለውጥ አርትን የመታገያ መሳርያ አድርጎ ለእርጅና የደረሰ፣ በመላ ሀገሪቱ በርካታ አድናቂና ተከታዮች ያሉት ሰው እንዲህ ያለውን ምላሽ መስጠቱ እንደ ተራ ጉዳይ የሚታይ አይደለም።

ከላይ እንደገለጽኩት ይህን ቃለ መጠይቅ በቀጥታ ያስተላለፈው የብልጽግና ፓርቲም ይሁን ሌላ ከጀርባው ሌላ አላማ ከሌለ በስተቀር የሟቾች ደም ባልደረቀበት በዚህ ሰአት በሺህ የሚቆጠሩ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ሀዘናቸውን ገና አምነው መቀበል ተስኗቸው የስነ ልቦና ጉዳት

በደረሰባቸው ወቅት እንዲሁም ኢትዮጵያ አይታና ሰምታ የማታውቀው እንዲህ ያለ በአንድ ብሄርና በተለይም በአንድ ሀይማኖት ላይ የተደረገ እልቂት ቶሎ እንድትረጋጋ ተቋማት ቁጭ ብድግ በሚሉበት ሰአት የዶ/ር አርቲስት አሊ ቢራ “ደግ አደረጉ” የሚል ንግግር ሌላ አመጽ ቀስቃሽ ከመሆኑም በላይ ድርጊቱን ፈጻሚዎች ከህሊና ወቀሳ እንዳይማሩ የሚያደርግ ማበረታቻ ነው።

በዚህ “የራስን ወንጀለኞች የማሞካሸት” አባዜና፣ የሌሎች ዜጎችን ሞት የዝንብ ያህል የመቁጠር አስተሳሰብ በየት በኩል ቢታከም ነው ህጋዊ መስመር ተከትለን እንደ ህዝብ ወንጀልን ወንጀል ብለን ፈርጀን ሀገርን ከዚህ አሳፋሪ ድርጊት ማዳን የምንችለው? የክብር ዶ/ር አርቲስት አሊ ቢራን ያህል ግዙፍ የመድረክ ሰው በዚህ ደረጃ ከገዳዮች ጎን መቆምስ የነገውን የህዝብ ለህዝብ አብሮ መኖር እንዴት ያወሳስበው ይሆን? መንግስትስ እንዲህ ያሉ የጥላቻ ንግግሮችና መልዕክቶችን በዚህ መልክ ሲተላለፉ ዝም ማለቱ ምን ያህል ተገቢ ነው? እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው!!

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *