Press "Enter" to skip to content

(title)

የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመው ጥቃት አጥፊዎችን በአንድ ጀንበር ድንገት ስሜት ቀስቅሷቸው የተከሠተ ሳይሆን ዝግጅት ሲደረግበት፣ ምክንያት ሲፈለግለት ቆይቶ የተፈጸመ መሆኑን የሚያመለክቱ ማሳያዎች አሉ።

አጥቂዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የጦር መሣሪያ ይዘው በመኪና ሲንቀሳቀሱ ከልካይ አለመኖሩ፣ የሚያጠቋቸውን ክርስቲያኖች ስም ዝርዝር አስቀድመው ማዘጋጀታቸው፣ ማንነታቸው እንዳይታወቅ ጭምብል ለማድረግ መሞከራቸው፣ ወደ ማይታወቁበት አካባቢ ተወስደው ጥቃቱን መፈጸማቸው ከጀርባ የሚያደራጅ አካል እንደነበረ የሚያመለክት ነው።

በሁለት ከተማ አስተዳደሮች፣ በኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ አሥር ዞኖች እና 45 ወረዳዎች የተፈጸመውን ጥቃት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት ሰብሳቢ እና ቤተ ክርስቲያን ተስፋ ልዑክ በሚል ያቋቋመችው ጸረ ኮቪድ-19 ግብር ኃይል ጸሐፊ የሆኑት ቀሲስ ሙሉቀን ብርሃኑ የገለጡት እንደሚከተለው ነው።

አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በድንገት ሕይወቱ ማለፉን እንደሰማን ጀዋር መሐመድ የተባለው ግለሰብ በዚህ ዓመት ጥቅምት ወር በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ ያሰራጨውን መረጃ (ተከበብኩ) ምክንያት በማድረግ በርካታ ምእመናን ሰማዕትነት እንደተቀበሉ እና ንብርታቸው እንደ ወደመ ስለምናውቅ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሚገኙ ዞኖች የሚኖሩ ክርስቲያኖች ራሳቸውን እና ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲጠብቁ አሳስበን ነበር፡፡ መልእክት ብናስተላልፍም ንጹሐን ምእመናን በጨካኞች የጥቃት ከመሆን እና ለበርካታ ዓመታት ያፈሩት ንብረት ከመውደም አላመለጠም፡፡

የአገራችን ሁኔታ የሚገርመው ፖለቲከኞችም ሆኑ አክቲቪስቶች በተሰለፉበት ሜዳ ሲሸነፉ ለንዴታቸው መወጣጫ የሚያደርጉት እንደ ጠላት የሚያይዋትን ቤተ ክርስቲያንን በማውደም ሽንፈታቸውን ለማካካስ መሰማራታቸው ነው፡፡ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ድንገተኛ ግድያ ሽፋን በማድረግ በኦርቶዶክሳውያን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ከእስከ አሁኑ ለየት የሚያደርገው ሟቹ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ሆኖ ሳለ አክራሪ ጽንፈኞች ግን በበደል ላይ በደል ምእመናንን እና ንብረታቸውን ያጠቁ ነበር፡፡ ጉዳዩን በጥልቀት ስንመረምረው በአሁኑ ወቅት ቤተ ክርስቲያናችንን የገጠማት ሁለት ጉዳት መሆኑን እንረዳለን፡፡

የአርቲስቱ ባለቤት እና እኅቶቹ በቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ ያደጉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የተፈጸመው ድንገተኛ የአርቲስቱ ግድያም ኦርቶዶክሳውያንን እያደኑ የመግደል ዕቅድ ያለው መሆኑን አመላካች ነው፡፡ በምእመናን ሕይወት እና ንብረት ላይ ጥቃት የፈጸመው ጽንፈኛ አክራሪ ኃይል የአርቲስት ሀጫሉ ሁዴሳ መሞት አሳዝኖት ኀዘኑን ለመግለጥ ሳይሆን ከኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች የጸዳ ኦሮሚያ ክልልን ለመመሥረት በማሰብ ሲያከናውነው የነበረውን ገሀድ ያወጣ ነው።

ለዚህም ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ጥቃቱ እጅግ በረቀቀና በተደራጀ ሁኔታ መፈጸሙን የሚያመለክተው አርቲስቱን ማን እንደገደለው ይፋ ሳይሆን ከሌለቲ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ምእመናንን እና ንብረቶቻቸውን ማጥቃት መጀመሩ ነው፡፡ ከኋላ ሆኖ ድርጊቱን ያስተባብርና ያደራጅ የነበረ ኃይል እንዳለም አመላካች ነው፡፡ ከወራት በፊት ተሰልቶና ታቅዶ የተቀመጠ ጥቃት መሆኑንም መረዳት ይቻላል፡፡

በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በመረዳት የተደራጀ ቡድን ቤተ ክርስቲያንን እና ምእመናንን እያጠቃ መሆኑን ለመንግሥት ስናሳውቅ ቆይተናል፡፡ የመንግሥት መልስ ግን “ቤተ ክርስቲያን እየተጠቃች ያለችው በተደራጀ ኃይል ሳይሆን በድንገተኛ ግጭት ነው” የሚል ነበር፡፡

የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ድንገተኛ ሞት ሽፋን በማድረግ የተፈጸመው ጥቃት የተደራጀ አክራሪ ጽንፈኛ ኃይል ቤተ ክርስቲያን እና ምእመናንን እያጠቃ መሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡ በዚህም የተደራጀው አክራሪ ጽንፈኛ የጥቃቱ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚገባ በብዙ ማስረጃ ከመንግሥት ጋር መግባበት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡ አንባብያን ከዚህ ንግግር ብዙ ቍም ነገሮችን ማውጣት ይቻላል። እስከ አሁን ስንጓዝበት የነበረውን መንገድ እንደገና ማየት እንደሞኖርብን ያስገነዝበናል።

አደጋ ሲደርስ አንድ ሰሞን ተንጫጭተን በመርሳት ሞት ነጥቆ የሚጨርሳቸውን የኃጥአን ምሳሌ የሆኑትን ፍየሎች መምሰል የለብንም። በንስሓ በመዘጋጀት በጎችን ፣ በዓለም ላይ ስንኖር በየዋሕነቷ የሰላም ምሳሌ የሆነችውን ርግብን እና ለአደጋ ቢጋለጥ ሌላውን አካሉን እንጂ ራሱን የማያስነካውን እባብን መምሰል ይኖርብናል።(ማኀበረ ቅዱሳን)

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *