Press "Enter" to skip to content

አስገኘው አሽኮ /አስጌ ዴንዳሾ/ ፖለቲከኞች ስራዬን ባልተገባ መንገድ በመተርጎም ስሜን እያጠፉ ነው አለ

ጨዋ እና አስተዋይ ህዝባችንን በማክበር ዳግም  የሰጠሁት ማብራሪያ። እንደሚታወሰው የወላይታን ህዝብ አስተሳሰብ የማይወክል የወረደ አመለካከት ያላቸው ጥቂት ግለሰቦች ስንኝ በመምዘዝ ሀሳብ እያዛቡ ለወላይታ ማንም ደፍሮ የማይጠቀመውን ቃል በመጠቀም ከእኔ ያጋጩ በመምሰል ህዝቡን ያላከበረ ብሎም የረከሰ ነገር በሶሻል ሚዲያዎች እየፈጸሙ ይገኛሉ።

ይህ ተግባራቸው በግልፅ የስም ማጥፋት ዘመቻ ቢሆንም አካሄዱ ግን ህዝብን በስህተት ትርጉም እየሰደቡ መሆኑ እኔን አስከፍቶኛል። በእርግጥም እኔን ብቻ የሚነካ ተግባር ቢሆን በዝምታ ባለፍኩ ነበር። ግለሰቦቹ ግን ህዝብን ለማሳነስ ዳዳቸው። በተለይም በዘፈኑ ግጥም ላይ ፈፅሞ ያልተጠቀሰ ስንኝ በመጨመር…

“አሳራ ዳዳ አይሶራ ዲኬ” ተብሏል በማለት ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት እና ልዩነት ለመፍጠር የሚጥሩ ግለሰቦች ስለመሆናቸው አስተዋይ ህዝባችን የሚረዳው ቢሆንም ዘፈኑ ተጠናቆ ሲለቀቅም ሊያደምጡት የሚችሉ በመሆኑ እውነታውን የሚደርሱበት ይሆናል።

“ሚዛራ ማዳ ማራራ ሚኬ
እና
“ካስቶሌ ካና ካጫና
ኩሼ ኢሚኬ ጋና”

የሚሉት ስንኞችም የተዛባ ትርጉም ተሰቷቸው አስተውያለሁ።  ከላይ የተጠቀሱትን ስንኞች ለብቻ በመምዘዝ የግጥሙን የረቀቀ ይዘት በማፍረስ እና የግጥሙን ሙሉ ሀሳብ በሚንድ መልኩ ስንኙን ከቀጥተኛ ትርጉሙ በማሸሽ ብሎም የቃሉን ታሪካዊ አባባልም ካለማስተዋል እና ካለማወቅ ከመነጨ አጉል ከሆነ አረዳድ በመነሳት ጨዋውን ህዝባችንን ለማስቀየም እና ለፖለቲካዊ ቁማር የህዝቡን ህልውና ሊደራደሩበት መጣራቸው አስነዋሪ ተግባር ስለመሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህንንም ነውር እያዩ በዝምታ ማለፍ ለኔ የበሉበትን ወጭት መስበር ሆነብኝ።

በእርግጥም ሙዚቃው ከተሰራ የቆየ ቢሆንም ለግምገማ ወደ ጎፋ ሳውላ ተልኮ በነበረበት ወቅት በድንገት ከእጃቸው አምልጦ የእስቱዲዮ የመጀመሪያ ቅጂው /Sample/ ወደ ህዝብ ሊደርስ ችሏል። ያም አሁን ካለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋ እንዲገጣጠም አደረገው እንጂ ሆን ተብሎ አልነበረም። ወደ ግጥሙ ስመለስ እኔ ግጥሙን የፃፍኩበት ቀጥተኛው መንገድ እንደሚከተለው ነው።

“ካስቶሌ ካና ካጫና
ኩሼ ኢሚኬ ጋና”

የሰው ነፍስ አልቆ የቁንጫና የውሻም ነፍስ እንገብራለን እንጂ እጅ አንሰጥም የሚል ቀጥተኛ ትርጉም ያለው ሲሆን

“ሚዛራ ማዳ ማራራ ሚኬ” የሚለው ደግሞ

ከትላላቅ ከብቶች ጋ ስንበላ ቆይተን እንዴት ከጥጃ ጋ እንበላለን የሚል የአማርኛ ቀጥተኛ ትርጓሜ አለው። በሌላ አገላለፅ ወይም ቅኔው ሲፈታ ሰሙ ሲገለጥ “ተመችቶን እየኖርን ሳለን ለምን ያነሰ ኑሮ እንመኛለን ” ወይንም “ደልቶን እየኖርን ከርመን ለምን የወረደ ኑሮ እንድንኖር እንፈቅዳለን፣ ድህነትንና ስንፍናን በላያችን ላይ ለምን እንጠራለን” የሚል ግልፅ የሆነ ሀሳብ አለው። በዚህ መልኩ እንደመረዳት እና የሚመጥነውን ተገቢ ትርጉም እንደመስጠት ያልሆነ ትርጉም በመጠቀም ሊያውም “ቆመንለታል” ለሚሉት ህዝብ ፈፅሞ የማይመጥን ጥጃ ነኝ ሌባ ነኝ ዓይነት ትርጓሜን በማበጀት ህዝብን ማሸማቀቅ ልክ አይደለም። ይህ ከ21ኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ የማይጠበቅ ኋላ ቀር አካሄድም ነው።

በዚሁ አጋጣሚ በግጥም መልክ በሙዚቃው የተጠቀሰውን ስንኝ ቃል በቃል የተናገሩት የጎፋ ንጉሥ የነበሩ ካዎ ካማ ለአጤ ምኒልክ ጦር እጅህን ስጥ በተባሉ ጊዜ እምቢኝ በማለት የተጠቀሙት ቃል ነው።

አንድ የኪነጥበብ ሰው የማንም ወገንተኛ ሳይሆን ለህዝብ የሚሰራ ህዝብ የሚያስተሳስር እና የሚያፋቅር እንጂ በወረደ ቃላት ህዝብ የሚነቅፍ አይደለም። እኔም ብሆን ያደኩበትን እና ያሳደገኝን የደቡብ ህዝብ መንቀፍ ይቅርና በየትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት የሚገኙ ዜጎችን በተለየ አይን ለማየት አልደፍርም። ማንነቴም አይደለም። ደቡብ ይኼን አላስተማረችኝም። ጨዋው ህዝቤም ይኼንን አልመከረኝም።
አስገኘው አሽኮ /አስጌ ዴንዳሾ/

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *