SHARE

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በፌስቡክ ገፃቸው ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኮቪድ19 ምን ሊያስከትል እንደሚችል በርግጥ መናገር አልቻለም። ሁኔታውን ተቋቁሞ ችግሩን በድል አድራጊነት እንድንወጣ የሚያስችሉን ሁለት ነገሮች አሉ፤ ቅድመ ዝግጅትና መመሪያዎችን ያለማመንታት ተፈጻሚ ማድረግ።

የመጨረሻው አስከፊ ሁኔታ ቢደርስ እንኳን ተዘጋጅተን መቆየታችን ጉዳቱን ይቀንሰዋል። ለዚህም የገንዘብና ሌሎች አቅርቦቶችን የማሰባሰብ ሂደትን ለማስተባበር ትናንትና ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴን አዋቅረናል። በፌደራል ደረጃ፣ ለይቶ የመከታተያ፣ ለይቶ የማቆያ እና የማከሚያ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል። ቀጣዩ ሥራ የሚያስፈልጋቸው ግብአት እንዲሟላላቸው ማድረግ ነው፤ የክልል መንግሥታትም ተመሳሳይ ዝግጅት ማድረግ ይቀጥላሉ።

ይህ ጊዜ ከድንጋጤ፣ ከፍርሃት እና ከጭንቀት ወጥተን ያሉንን ግብአቶች ሁሉ አሰባስበን ወደ ብሔራዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያው በመጨመር አስተዋጽኦ እናድርግ።

ገንዘብ ለማዋጣት እንዲቻለን የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች እና የአጭር ጽሑፍ መላኪያ ሥርዓቶች ተዘጋጅተዋል።ታታሪ አርሶ አደሮቻችን እና የምግብ አምራቾች የምግብ አቅርቦቶችን መለገስ እንዲችሉ የምግብ ባንክም በመዘጋጀት ላይ ነው። እጅግ ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎቻችን የሚያስፈልጉ ሸቀጦችን የማዘጋጀት ሥራው እንዳለ ሆኖ፣ ለይቶ የመከታተያ፣ ለይቶ የማቆያ እና የማከሚያ ማዕከላት የሚያስፈልጓቸውን መሣሪያዎች ማሟላትም ይጠበቅብናል።

መከራ በገጠመን ጊዜ በአብሮነት እንደምንጋፈጠው በተግባር እናሳይ። ኢትዮጵያ ብለን ለምንጠራት የጋራ ቤታችን እያንዳንዳችን አስተዋጽኦና ኃላፊነት አለብን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here