SHARE

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች የተወሰነውን ውሳኔ በተሳሳተ መንገድ የሚተገብሩ ተቋማት መኖራቸው ተገለጸ።

የከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ሓላፊ አቶ ሃይሉ ሉሌ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ለመንግስት ሰራተኞች የተሰጠውን እረፍት እና ተያያዥ ጉዳዮች በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም የጤና ፣ የአገልግሎት ፣ የኮንስትራክሽን እና የመንገድ ዘርፍ ሰራተኞች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በስራ ገበታቸው ላይ በመገኘት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ሓላፊው ገልጸዋል፡፡

የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የወሳኝ ተቋማት ሰራተኞች መንግስት ያሳለፈውን ውሳኔ ችላ የማለት እና ህብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን አገልግሎት ከመስጠት አንጻር አብዛኛው ሰራተኞች ከስራቸው የመቅረት ዝንባሌ መታየቱን ሓላፊው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ለአብዛኛው የመንግስት ሰራተኞች በቤታቸው ሆነው እረፍት እንዲያደርጉ ቢወሰንም የተወሰኑ ስራተኞች በሽታውን በይበልጥ በሚያስፋፋ መንገድ በተለያዩ መዝናኛ እና የገበያ ስፍራዎች ጊዜያቸውን በማሳለፍ ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

በተለይ በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የጤና ዘርፍ ተቋማት ፣የምግብ፣ምድሃኒት እና ጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን ፤ ከአገልግሎት ዘርፎች የእሳት አደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ፣የውሃ እና መብራት አግልግሎት ፣የህብረት ስራ ማህበራት ፣የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች እንዲሁም የጥበቃ ሰራተኞች በሙሉ በመደበኛ ስራቸው ላይ እንደሚቆዩ አቶ ኃይሉ አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም የኮንስራክሽን እና የመንገድ ዘርፍ በሳይት ስራ ላይ የሚሰሩ ሙሉ ሰራተኞች በስራ ላይ እንደሚቆዩ የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በማዕከል፣ በክፍለ ከተማ እና ወረዳ ድረስ ከ65 እስከ 75 በመቶ የመንግስት ሰራተኞች ከቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ መወሰኑ የሚታወስ ነው ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here