SHARE

ገዳዩ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከአካላዊ ንኪኪ እራቁ ቢባልም በአዲስ አበባ አሁንም ማሳጅ ቤቶች እና የፍል ውሃ አገልግሎቶች እንደቀጠሉ ናቸው።

የኮሮና ቫይረስ ገና ኢትዮጵያ ሳይገባ ስለቫይረሱ መተላለፊያ መንገዶች አስቀድሞ ነበር ማስተማር የተጀመረው።

ትምህርቱ በመገናኛ ብዙሃን አስቀድሞ ለህዝቡ መነገር የተጀመረው ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ እንደማይቀር ስለተገመተ ነበር።

በመጨረሻም የጠበቅነው አልቀረም ከሁለት ሳምንት በፊት የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ተገኝቶ በኢትዮጵያ የተጠቂዎች ቁጥር 12 ደርሷል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የተጠቂዎች ቁጥር መንግስት በይፋ ካሳወቀው ሊበልጥ እንደሚችል የብዙዎች እምነት ነው።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ስለ ኮሮና መከላከያ ስራዎች እና እርምጃዎች በስፋት መነገር ተጀምሮ ይሄው መንግስትን ስራ እስከማቆም አድርሶታል።

አካላዊ ንኪኪአለማድረግ፣ርቀትን መጠበቅ እና እጅ መታጠብ ዋነኛ መፍትሔ እንደሆነም በየቀኑ የሚነገር የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶች ናቸው።

ኢትዮ ኤፍ ኤም በተለይም አካላዊ ንኪኪ የግድ የሆነባቸው የመዝናኛ አገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዴት እየሰሩ ነው ሲል በአዲስ አበባ የተለያዩ ሰፍራዎች ምልከታ አካሂዷል።

ምልከታ ያካሄድንባቸው ተቋማትም የማሳጅ ቤቶች እና ፍልውሃ ዋነኞቹ ነበሩ።

በምልከታችን እንዳረጋገጥነው ምልከታ ካካሄድንባቸው 6 የማሳጅ ቤቶች ከአንዱ በቀር አካላዊ ንኪኪ እንዳይፈጠር የሚያደርጉ የመከላከያ መንገዶችን ማለትም የፊት መሸፈኛ፣ጓንት እና ሌሎች የንጽህና መጠበቆያዎች እንደሌሉ አረጋግጠናል።

ፍልውሃ አገልግሎትም ከፍተኛ የሰው መተፋፈግ ባለበት ሁኔታ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ መሆናቸውን ታዝበናል።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭን መከላከል ስራዎችን የሚያስተባብረው የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት አለው? ስንል ጠይቀናል።

በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የአለም አቀፍ የጤና ደንብ የኢትየጵያ ተጠሪ ዶክተር ፈይሳ ረጋሳ ከእኛ የሚጠበቀው ህብረተሰቡን ማስተማርና ለመንግስት ምክር ሀሳብ ማቅረብ ነው ፣ ጠቅላይ ሚስሩም ምክር ሀሳብ መመሪያ አድርገው ለህዝቡ አስተላለፈዋል ፣ ተግባራዊ አለመደረጉ ግን ታዝበናል ብለዋል፡፡

እኛ ሀላፊነታችን ተወጥተናል የማሳጅ ቤቶች እና ጭፈራ ቤቶች እንዲዘጉ አስወስነናል ፣ ውሳኔው እንዲተገበር የከተማ አስተዳደሩ እና ፖሊስ የወጣውን መመሪያና ጠቅላይ ሚስትሩ ያስተላለፉትን መልዕክት ማስፈፀም እንዳለባቸው ዶክተር ፈይሳ ተናግረዋል፡፡

አሁንም ህብረተሰቡ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ሲካሄድ አካላዊ ርቀቱን ጠብቆ መንቀሳቀስ አለበት ፣ የንፅህና መጠበቂያ ለመግዛት የሚደረገው አላስፈላጊ ሰልፍ በእራሱ ለቫይረሱ ስርጭት አጋላጭ ነው በመሆኑም ሁሉም ሰው ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡

ምንጭ፡ ኢትዮ ኤፍ ኤም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here