Press "Enter" to skip to content

በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ይሥሐቅ ዘመነ መንግስት (1414-1429) እንደተቆረቆረች የሚነገርላት የሬማ መድሐኒዓለም ወለተ ጴጥሮስ አንድነት ገዳም

Last updated on March 26, 2020

በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ይሥሐቅ ዘመነ መንግስት (1414-1429) እንደተቆረቆረች የሚነገርላት የሬማ መድሐኒዓለም ወለተ ጴጥሮስ አንድነት ገዳም መሰራች አቡነ ኖቭ ነበሩ፡፡ ገዳሟ የክብ ቅርጽ አሠራርን የተላበሰች ሆና ቅኔ ማህሌቷ ጣራውን ደግፍው ዙሪያውን በቆሙ 19 የእንጨት ቋሚዎች የተሰራች እንደነበር ይነገራል፡፡

ቅድስትና መቅደሷ ከድንጋይ እና ጭቃ፣ ጣሪያዋ ደግሞ በእንጨት የተሰራ፣ ክዳኗ ሣር የለበሰች ሀኖ የተሠራች ጥንታዊ ገዳም እንደነበረች ይነገራል፡፡ ገዳሟ ከባሀርዳር ከተማ በሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ በጣና ሐይቅ 3፡00 ሠዓት የባህር ላይ ጉዞ በኋላ በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ በምዕራፍ ማርያም ቀበሌ ትገኛለች፡፡

የገዳሟ የውስጥ ግድግዳዎች በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተሳሉ በሚነገርላቸው የሐይማኖታዊ ሥዕላት የአሸበረቀ የነበረ በመሆኑ ገዳሟ እጅግ ሳቢና ማራኪ እንደነበረች አሁን ፈራርሰው በሚገኙት ሥዕሎቿ ይታወቃል፡፡

የሬማ መድሐኒዓለም ወለተ ጴጥሮስ አንድነት ገዳም አካባቢውን ያስዋቡት አገር በቀል ደኖች መካከል እና ዙሪያዋን በጣና ሐይቅ ተከባ የምትገኝ ስትሆን ግቢውም ባማሩ ዕጽዋት የተሸፈነ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ገዳሟ በርካታ ቅርሶች እንዳሏት ይነገራል፡፡ ከነዚህም መካከል በገዳሟ የኖሩ የነበሩ መነኮሳት ይጠቀሙባቸው የነበሩ ገንዳዎችና ሙቀጫ፣ጥንታዊ የብራና መጽሐፍት፣ነዋየ ቅድሳት፣የአፄ ሠርፀድንግል አጽምና አልጋ፣የተለያዩ አባቶች እና ነገስታት አፅሞች ይጠቃሳሉ፡፡

አሁን ያለው የገዳሙ ሀንጻ በኮንክሪት የተሰሩ 19 አምዶች፣የቅድስቱ 4 ትልልቅና 4 ትንንሽ ከእንጨት የተሰሩ በሮች፣8 ከእንጨት የተሰሩ መስኮቶች ያሉት ሲሆን፣መቅደሱ ደግሞ 3 ከእንጨት የተሰሩ በሮችና አንድ መስኮት አሉት፡፡

ገዳሟ ቅኔ ማህሌት፣ቅድስትና መቅድስ የሚባሉ ክፍሎች ሲኖሯት በ1989 ዓ.ም የቅድስቱን ግድግዳ በሲሚንቶ የመተኮስ ስራ ተሰርቷል፡፡ ይህም የቤተክርስቲያኑን ህንጻ ውብት ከማበላሸቱም በላይ የቅርስነት ይዘቱን እንዲያጣ አደርጎታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በ1997 ዓ.ም የቅኔ ማህሌቱን ቋሚ እንጨቶች በመነቃቀል በኮንክሪት ምስሶዎች(ኮለን) ለመተካት በተደረገው ሥራ በገዳሟ ህንጻ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ተደርጓል፡፡

በ1984 ዓ.ም ደግሞ ሣር የነበረውን የጣራ ክዳን በመቀየር ቆርቆረ እንዲለብስ ተደርጓል፡፡

የገዳሟ ቅድስት የውስጠኛው ግድግዳ የነበሩት ቅዱሳን ሥዕላት በምስጥ በመበላታቸውና በዕድሜ ብዛት፣ የጥገናና እንክብካቤ እጦት የተነሳ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፡፡ በገዳሟ ሲኖሩ የነበሩ መነኮሳት ሲጠቀሙበት የነበረ ገንዳ እና ሙቃጫም በምስጥ በመበላቱ ከጥቅም ውጪ ሊሆን ተቃርቧል፡፡

ሌሎች ጥንታዊ በራና መጽሐፍትና ንዋየ ቅድሳት ቅርሶችም የአካባቢው ማህበረሰብ ባለመስማማትና ባመተማመን የተነሳ በአንድ ከፍል ውስጥ አየርና የጸሐይ ብርሃን በማያገኙበት ሁኔታ ተቆልፈው እንደሚገኙ ሰምተናል፡፡

የዚህ ዓይነቱ የቅርሶች አያያዝና አጠባባቅ በአካባው ያለው ከፍተኛ የአየር እርጥበት፣ በራሪ ነብሳትና የመሬት ተባዮች(ምስጥ) ተዳምረው ለህንጻዎቹም ሆነ በውስጧ ለሚገኙ ቅርሶች መበላሸት አይነተኛ ምክንያቶች ናቸው/ለብልሽት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ያመላከታል፡፡

ገዳሟ ከተሠራች በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረች በመሆኗ ጥገናና እንክብካቤ ሳይደረግላት በመቆየቱ አሁን ላጋጠማት የመፍረስ አደጋ ተጋልጣለች፡፡ ለቅርሶች የሚደረግ ጥገና ዕውቀትን የሚጠይቅ ቢሆንም ዕውቀቱም ሆነ ግንዛቤ በሌላቸው ግለሰቦች ጥገና ለማድረግ በመሞከሩ ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጣለች፡፡ ለረጀም ጊዜ/እስከነአካቴው በባለሙያ የተደገፈ ጥገናም ተደርጓላት አያውቅም፡፡

በገዳሟ ላይ የተደረጉ ጥገናዎች የቅርስ ጥገና ሙያ ከሚጠይቀው ክህሎት ውጭ የተከናወኑ በመሆናቸው በመካነ ቅርሱ የቅርስነት እሴት ላይ አሉታዊ ውጤት የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ ለጥገና የዋሉ ቁሳቁሶች የቅርሱ ጥንታዊነት የጠበቁ አይደሉም፡፡ በሲሚንቶ ቅጥራን ጥገና ለማድረግ በመሞከሩ የሲሚንቶው ቅጥራን የገዳሟን ህንጻ በእጅጉ ከመጉዳቱም በላይ ለእይታም አይችም፡፡

ጥገናው ከጥንቱ ቤተክርሲተያን ህንጻ አሠራር ጋራ አብሮ የማይሄድ በመሆኑ የቅርስነት ፋይዳውን ከመቀነሱም በላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ የገዳሟ የጣራ ክዳን ከሣር ወደ ቆርቆሮ የተቀየረ ሲሆን ለግድግዳ ጥገና የዋለው ቅጥራን /የጥገና ቁስ/ በሲሚንቶ የተተካ ነው፡፡ይህ ለቅርስነት እሴት ተገቢ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን ራሱን የቻለ ጉዳት የሚያስከትል ነው፡፡

ገዳሟ ስትሠራ የነበሩ በሮችና መስኮቶች ተነስተው አንዳንዶቹ በመናኛ የእንጨት በሮች መተካታቸው የመካነ ቅርሱን ምሎዕነት እና ወጥነት ቀንሶታል፡፡
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ቅርሱ ከእድሜ ብዛት እና ከጥገናና እንክብካቤ እጦት እንዲሁ ከግድየለሽነት የተነሳ በመጉዳቱ እየፈረስ ይገኛል፡፡ ከዘመን ብዛት እና በምስጥ በመቦርበሩ ህንጻው እየጠሰነጣጠቀ የመፈራረስ አደጋም እየገጠመው ነው፡፡

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *