Press "Enter" to skip to content

“ልጄ ከነ ማተቧ ተወልዳለች፤ በማየትም መረዳት ይችላሉ::” ወላጅ እናት

በቅርቡ በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ማተብ አንገቷ ላይ አድርጋ ተወለደች የተባለቸዋ ሕጻን የማኅበራዊ ሚዲያዎች መነጋጋሪ ሆናለች፡፡ አብመድም የዳንግላ ወረዳ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትን ዘገባ ዋቢ አድርጎ መረጃውን ለአንባብያን አድርሶ ነበር፡፡ የሰሚ ሰሚ መረጃ አድርሶም ዝም አላለም አብመድ ወደ ሕጻኗ ዘንድ በመሄድ ተመልክቷል ሰዎችንም አነጋግሯል፡፡

ተአምረኛዋን ሕጻን ለማየት አብመድ ብቻም ሳይሆን የአካባቢው ነዋሪዎች የቅርብ ዘመድ አዝማድ እና የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ወደ ዳንግላ ወረዳ ውፍጣ ዳጢ ቀበሌ አቅንተዋል፡፡ ውፍጣ ዳጢ ቀበሌ ከወረዳው ዋና ከተማ ዳንግላ በ1አስራ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት በስተ ምዕራብ አቅጣጫ ይገኛል፡፡ እኛም ሕጻኗ ጋር አብሮ ተወልዷል የተባለውን ማተብ ለማየት በአካባቢ የደረሱ ሰብሎች የሕጻናትን ጨዋታ የከብቶችንና የአእዋፋትን ዝማሬ እያዬን እና እየሰማን ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ ውፍጣ ዳጢ ቀበሌ ደርሰናል፡፡

እንደ ደረስንም የመጀመሪያ ልጇን በሠላም ከተገላገለችዋ ወጣት ወይዘሮ ጥሩወርቅ አብነት ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል፡፡ በ2010 ዓ.ም ነው ትዳር የመሠረተችው፡፡ ከአራት ጊዜ የቅድመ ወሊድ ሕክምና ክትትል በኋላ በወርሃ ጥቅምት በ27ኛው ቀን 2012 ዓም ከለሊቱ ስምንት ሰአት የበኩር ልጇን በሐኪሞች እገዛ ተገላገለች፡፡ በወሊድ ጊዜም ከምሽቱ ሁለት እስከ ስምንት ሰዓት ምጥ ላይ ቆይታለች፡፡

በወሊድ ጊዜ ተጨናንቄ ነበር ማተብ ይኖራል ብዬ ወዲያውኑ አላየሁትም በጣም አሞኝም ነበር፡፡ መብራትም አጋጣሚ አልነበረም፡፡ ገላዬን ታጥቤ ሕጻኗን ጡት ላጠባት ከእናቴ ስቀበላት ነው ያየኋት ነው ያለችው ወይዘሮ ጥሩወርቅ፡፡

ወዲያውኑ ባያት ኖሮ አንገቷን ያንቃታል ብዬ እበጥሰውም ነበር እንዳየሁም ለጊዜው ደንግጫለሁ አሁን ግን ደስተኛ ነኝ ስትል ተናግራለች፡፡ በሕጻኗ አንገት ላይ ማተቡን እንዳየችው ለማንም ለመናገር ያልደፈረችበትን ምክንያትም እስከ ክርስትና ድረስ በይፋ ላለመናገር አስባ እንደነበር የገለጸችው እናት አሁን ግን ፈጣሪ ለዓለም ምሳሌ አድርጓት እንደሆነ አስባለሁ ታሪኳን ለሚጠይቀው ሰው ሁሉ ከመናገር ወደ ኋላ አልልም ብላለች፡፡

እኛም ስንመለከት በሕጻኗ አንገት ላይ ያለው ማተብ ምንም ዓይነት ቋጠሮ የለውም፡፡ የሰው ቆዳ የሚመስል ጉንጉን ነገር ነው ውኃ ሲነካው ይለጠጣል ውኃ ካልነካውና ካልተለጠጠ መውለቅ አይችል ከሕጻኗ ሰውነት ጋርም አልተያያዘም፡፡

ይህንን ማተብ እናንተ ያሠራችሁት ምልክት ቢሆን እንዴት ማመን እንችላለን ሲል አብመድ ለእናቲቱ ጥያቄ አንስቷል። በእምነታችን ወንድ በአርባ ሴት ደግሞ በሰማንያ ቀን ማተብ እንደሚታሠርላቸው እናውቃለን። የእምነት አባቶችም አስተምረውናል ፈጣሪ ቋጥሮ የሰጠኝ ልጅ ናት እኔና እናቴ እናውቃለን። ይህንን የሚሉ ሰዎች በማየት መረዳት ይችላሉ ብላለች ወይዘሮ ጥሩወርቅ፡፡

ማተቡም የሚጠፋብኝ ስለ ሚመስለኝ አላወልቀውም እስከ ሕይወት ዘመኗ አብሯት ይኖራል ብላለች፡፡ ጉዳዩን የሰሙት ጓደኞቿ ጎረቤት የቀበሌው ነዋሪዎች እና የተለያዩ ሚዲያዎች እየመጡ እየጎበኟቸው ነው፡፡

ወይዘሮ ማጫሽ ይመኑ የወይዘሮ ጥሩወርቅ እናት ናቸው፡፡ በወቅቱ ልጃቸው ስትልድ ከጤና ጣቢያው ነበሩ፡፡ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስረዱ ሕጻኗ ከማሞቂያ ቤት ስትሰጠኝ የሆነ ነገር አየሁ። ዝቅ ብየ ስመለከትም ማተብ ነው እስኪነጋም ለማንም አልተናገርሁም።

ልጄ ጥሩወርቅ ስትጠይቀኝ ‹ፈጣሪ ታምር ሊያሳየን የሠራው ሥራ ነው ዝም በይ ነው ያልኃት ብለዋል፡፡ ሕጻኗ ከማሞቂያ ውስጥ ወጥታ መጀመሪያ ለእርሳቸው እንደተሰጠቻቸው እና ከፈጣሪ የተሰጠ ማኅተምም ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ ማንም ያልቋጠረው ትክክለኛ ማተብም እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የወፍጣ ዳጢ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ሰውነት የወይዘሮ ጥሩወርቅ ወንድምና ጎረቤት ናቸው፡፡ በቅርበት ሆነው እርሳቸውም ዘግይተው ጉዳዩን እንደሰሙት አጫውተውናል፡፡ አራስ ለመጠየቅ ሄደው የተለየ ነገር በማየት ለማኅበረሰቡ እና ለሚመለከተው አካል መናገራቸውንም አስረድተዋል፡፡ መጀመሪያ ከቤተሰብ ውጭ መረጃው ለሌላ ሰው የደረሰው በእርሳቸው በኩል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች እና ለሌሎችምች ሕጻኗን እየጎበኟት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ባለማተቧ ልጅ ከመወለዷ በፊትም እዚህ አካባቢ ማተብ ያላት ልጅ ትወለዳለች ማተቧንም አትበጥሱ ለዓለምም ምሳሌ ትሆናለች የሚል ትንቢታዊ መልዕክት ከወለተ ጴጥሮስ ገዳም ከሚኖሩ የሃይማኖት አባት ለአካባቢው ሰዎች እንደተነገረም ሰምተናል። ትምቢቱም ተፈፅሟል ብለዋል አቶ ተፈራ፡፡

ሕጻኗ የተወለደችበት የአባድራ ጤና ጣቢያ አዋላጅ ነርስ አቶ እውነቱ አብየ ደግሞ ወይዘሮ ጥሩወርቅ ተገቢ የቅድመ ወሊድ የሕክምና ክትትል ስታደርግ እንደነበረ እና በሠላም መውለዷን አረጋግጠውልናል፡፡

ከተወለደች በኋላ ግን ሕጻኗን በፎጣ ጠቅልለን ማሞቂያ ውስጥ ነው ያስገባናት ብለዋል፡፡ አቶ እውነቱ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስረዱም በወሊድ ወቅት ወይዘሮ ጥሩወርቅ ላይ የማኅፀን በር ላይ መጠነኛ መሰንጠቅ ስለ ነበር ሕክምና ለመስጠት ነው ተጣድፈን የነበረው። ሕጻኗ ስትወለድ ምንም ልዩ ምልክት አላየሁም ቆይተን ስንሰማ ግን ሕጻኗ ማተብ ያላት መሆኗን እንደማንኛውም ሰው ነው የሰማሁትና ያየሁት ብለዋል፡፡

በወሊድ ጊዜ ይህ ክስተት መኖሩን ባውቅ ኖሮ አንገቷን ያንቃታል ብዬ እበጥሰው ነበር ግን በወቅቱ አላየሁትም ሕጻኗ በሠላም በመወለዷ ደስተኛ ነኝ ብለዋል፡፡ አብመድ ያነጋገራቸው በዘርፉ የሚሠሩ የሕክምና ባለሙያዎች ደግሞ የሕጻኗን የእትብት እና ከአንገቷ ላይ ያለው የማተብ ናሙና በቤተ ሙከራ ላብራቶሪ ምርመራ ተርጋግጦ መታወቅ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ለጉዳዩም እስከ ቦታው በመሄድና በማርጋገጥ በቅርቡ ምላሽ እንደሚሰጡ ለአብመድ ቃል ገብተዋል፡፡ አብመድ

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *