Press "Enter" to skip to content

cማስተርካርድ ፋውንዴሽን በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ መክፈት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ

ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ለመክፈት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌ እና በኢትዮጵያ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ተወካይ አለማየሁ ኮንዴ ተፈራርመውታል።

ሚኒስትር ዲኤታው ኢትዮጵያ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ጠቅሰው፥ ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በአዲስ አበባ ቅርንጫፉን ለመክፈት መወሰኑ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

ፋውንዴሽኑ ሴቶችንና ወጣቶችን ለማብቃት መንግስት ለነደፈው ግብ መሳካት ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል።

የማስተርካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ተወካይ አለማየሁ ኮንዴ በበኩላቸው፥ መንግስት ቢሮ እንዲከፍቱ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ፋወንዴሽኑ በግብርና፣ ማምረቻው ዘርፍ፣ ቱሪዝም፣ ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የፋይናንስና ቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ፥ ኢትዮጵያን ከተመረጡ 10 ስትራቴጂክ ሀገራት አንዷ አድርጎ መምረጡንም አስታውቀዋል፡፡

አያይዘውም ፋውንዴሽኑ ከስራ ፈጠራ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በሚቀጥሉት 10 አመታት በርካታ የስራ እድሎችን ለማመቻቸት መወጠኑን ገልጸው፥ ከዚህ ውስጥ 70 ከመቶ የሚደርሰው ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተለየ ነው ብለዋል።

ማስተርካርድ ፋውንዴሽን በፈረንጆቹ 2006 በካናዳ የተመሰረተና ለትርፍ ያልተቋቋመ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።

በዚህም በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት ያሉ ወጣቶች በትምህርትና በስራ ብቁ ሆነው ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ዓላማውን ያደረገ ዓለም አቀፍ ድርጅት መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *