Press "Enter" to skip to content

ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተሰጠ ማስጠንቀቅያ

የክረምት ዝናብን ተከትሎ በአብዛኛው ከመስከረም እስከ ታህሳስ ወር ዋነኛ የወባ መተላለፊያ ወቅት መሆኑንና ህብተሰቡ ቀድሞ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕይወት ሰለሞን አሳስበዋል፡፡ 75 በመቶ የሚሆነው የሀገራችን ክፍል ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ ሲሆን 60 በመቶ የሚሆነው ህዝብም በእነዚህ አካባቢዎች ይኖራል፡፡
.
በመሆኑም ህብረተሰቡ አጎበር እንዲጠቀም፣ የበሽታው ስሜት ሲኖር ቶሎ ወደ ህክምና መስጫ ማዕከላት እንዲሄድ እንዲሁም ለወባ በሽታ አምጪ ትንኝ መራቢያ አመች የሆኑ የታቆሩ ውሃዎችን ማፋሰስና ማዳረቅ የሚጠበቅ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሯ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ክልሎች፤ ዞኖች፤ ወረዳዎችና የጤና ተቋማት የተጠናከረ የወባ በሽታ ክትትልና ቅኝትን በቀጣዮቹ ወራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ አክለውም ከስር በዝርዝር የተጠቀሱትን ቁልፍ ተግባራት በየደረጃው ትኩረት ሰጥተው ማከናወን እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

• ወቅቱንና ነባራዊ ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ በወባ በሽታ መከላከል፣ መቆጣጠርና ማስወገድ ላይ ያተኮሩ የተለያዩ መልዕክቶችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ በሆኑ ልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን ወቅቱን ጠብቆ በማስተላለፍ የህብረተሰቡን ግንዛቤና ንቃተ ጤና እንዲጨምርና የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ማድረግ፣

• የተሰራጩ የመኝታ አልጋ አጎበሮችን ህብረተሰቡ በትክክል እንዲጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እንዲሰራ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ፣

• ቤት ውስጥ የፀረ-ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት በመመሪያው መሰረት በተመረጡ ቀበሌዎች ወቅቱን ጠብቆ እንዲረጭ ማድረግና ፤ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ፣

• በወባማ አካባቢ የሚገኙ ጤና ተቋማት በቂ የሆነ የወባ መድኃኒትና ሌሎች ግብዓቶች እንዲኖራቸው ማድረግ (እንዳይቆራረጥም አስፈላጊዉን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ)፣

• ወቅታዊ/ሳምንታዊ የወባ ህሙማን ሪፖርትን ማጠናቀር፤ መተንተን፤ የወባ ወረርሽኝ መከታተያ ቻርትን /Epidemic monitoring chart/ እንዲጠቀሙ ድጋፍ ማድረግ፣

• የወባ ህሙማን ቁጥር መጨመር የሚታይባቸዉን ወረዳዎችን/አከባቢዎችን በመለየት የወባ ወረርሽኝ እንዳይከሰት በየደረጃው ፈጣን ግብረ-ሀይል (Rapid Response Team) በማቋቋም የቁጥጥር ስራ መስራት ያስፈልጋል፡፡

እስካሁን በተከናወኑ ተግባራት ባለፉት14 ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ ምንም የወባ በሽታ ወረርሽኝ አልተከሰተም፡፡

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *